የሸህ መሀመድ ሁሴን አል አሙዲ ንብረት ከሆነው ከሚድሮክ ጎልድ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መንግስት ማጣቱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሲያጋልጥ፤ ሚድሮክ ጎልድ በበኩሉ 10 ሳንቲም ዕዳ የለብኝም ሲል አስተባበለ።

ሰኔ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ግን ማስተባበያውን አጣጥለውታል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት፣ የማዕድን ሚኒስቴር የሼክ መሐመድ አል አሙዲ የወርቅ ልማት ኩባንያ ከሆነው ሚድሮክ ጐልድ በሕግ የተወሰነውን ገቢ ባለመሰብሰቡ፣ አገሪቱ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ አጥታለች ማለቱ ይታወሳል።
ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ በማዕድን አዋጁ 78/2002 መሠረት በከፍተኛ የማዕድን አምራቾች ላይ ስምንት በመቶ የሮያሊቲ ክፍያ፣ እንዲሁም በመካከለኛ የማዕድን አምራች ኩባንያዎች ላይ መንግሥት አምስት በመቶ ነፃ የአክሲዮን ድርሻ እንደሚኖረው ቢደነገግም፣ የማዕድን ሚኒስቴር ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም. ባሉት የበጀት ዓመታት ከሚድሮክ ጐልድ የሰበሰበው የሮያሊቲ ክፍያ አምስት በመቶ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም ከመንግሥት ነፃ የአክሲዮን ድርሻ ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑን በማዕድን ሚኒስቴር ላይ በተካሄደው የክዋኔ ኦዲት ቁጥጥር መረጋገጡን ዋና ኦዲተሩ ለፓርላማ ሪፖርት አድርገዋል፡፡
ፓርላማው ካፀደቀው የሮያሊቲና የመንግሥት ድርሻ ምጣኔ ውጪ ሚኒስቴሩ ሚድሮክ ጐልድን በዝቅተኛ ምጣኔ በማስከፈሉ፣ መንግስት በድምሩ 429 ሚሊዮን ብር ገቢ ማጣቱን ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው አመልክተዋል።
የሚድሮክ ጐልድ ዋና ሥራ አስኪያጅና የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አረጋ ይርዳው በሰጡት ማስተባበያ፦‹‹ኩባንያው ሕግን አክብሮ ኃላፊነቱን የሚወጣ ድርጅት ነው፡፡ አሥር ሳንቲም የመንግሥት ዕዳ የለበትም፤›› ብለዋል፡፡
ዶክተር አርጋ ሚድሮክ ጐልድ የማዕድን አዋጅ ቁጥር 52/1985 መሠረት በማድረግ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር የ20 ዓመታት የማዕድን ማውጣት ውል መግባቱን፣ በውሉ መሠረትም አምስት በመቶ የሮያሊቲ ክፍያና ሁለት በመቶ ነፃ የአክሲዮን ድርሻ በኩባንያው ላይ እንዲኖረው መደረጉን በደብዳቤያቸው አብራርተዋል፡፡
ቀደም ብሎ ለ20 ዓመታት የተገባን የውል ስምምነት አዲሱ አዋጅ ሊቀይረው አይገባም በማለት፣ ሚድሮክ ጐልድ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ለሦስት ዓመታት የተከራከረ መሆኑን ያውሱት ዶክተር አረጋ፤ በመጨረሻም ሚኒስቴሩ በሚድሮክ ጐልድ አቋም መስማማቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ጥር 28 ቀን 2005 ዓ.ም. መላኩን እና ሚድሮክ ጐልድ በገባው ውል መሠረት እንዲቀጥል መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ‹‹በሚድሮክ ጐልድ ላይ የኦዲት ቁጥጥር አናደርግም፡፡ ቁጥጥር ያደረግነው በማዕድን ሚኒስቴር ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ይህ ቢሆንም በኦዲት መርህ መሠረት ተገቢው ምርመራ በሚኒስቴሩ ላይ መደረጉንና ለ20 ዓመታት የተደረገውን ውል መሠረት በማድረግ ተደርጐ የነበረውን ክርክርና የተሰጠውንም እልባት መመርመራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዋና ኦዲተሩ አክለውም፦‹‹ፓርላማው ያወጣውን ሕግ፤ ማዕድን ሚኒስቴር በደብዳቤ ሊቀይረው አይችልም፡፡ ፓርላማው ራሱ በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኃላፊነት ደግሞ የመንግሥት ተቋማት ሕግን አክብረው መሥራታቸውን ተቆጣጥሮ ለፓርላማው መረጃ ማቅረብ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በመሆኑም ማዕድን ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 678/2002 አንቀጽ 81 ላይ፣ ‹‹ይህ አዋጅ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የተሰጠ ፈቃድ ወይም የተደረገ የማዕድን ስምምነት ከዚህ አዋጅ ጋር እስካልተቃረነ ድረስ ፀንቶ ለሚቆይበት ቀሪ ዘመን ተፈጻሚነቱ ይቀጥላል፤›› የሚለውን አንቀጽ ተላልፏል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ማዕድን ሚኒስቴር ይህንንና ሌሎች በኦዲት የተለዩ የአሠራር ችግሮቹን ለማስተካከል የድርጊት መርሐ ግብር አውጥቶ ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት እንዲልክና መንግሥት ከሚድሮክ ጐልድ ያጣውን ገንዘብ እንዲያስከፍል አሣስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓርላማው በ2006 ዓ.ም. በማዕድን አዋጁ ላይ ባደረገው ማሻሻያ፣ በኢትዮጵያ በከፍተኛ የማዕድን ልማት ብቸኛ የሆነውን ሚድሮክ ጐልድን የመከራከሪያ ነጥብ የተገነዘበ ማስተካከያ አድርጓል፡፡