ኢሳት (መጋቢት 29 ፥ 2009)
አሜሪካ የሶሪያው ፕሬዚደንት ባሽር አልአሳድ ከስልጣን የሚወገዱበት ሁኔታ መታየት ወዳለበት አማራጭ መድረሱን ይፋ አድረገች።
በሶሪያ መንግስት ከቀናት በፊት በንጹሃን ሰዎች ላይ ጥቅም ላይ ውሏል በተባለ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ግድያ ተቃውሞዋን ስታሰማ የሰነበተችው አሜሪካ ፕሬዚደንት አሳድ ስልጣናቸው በሃይል የሚያከትምበት ጊዜ መቃረቡን ለመጀመሪያ ጊዜ ፍንጭ መስጠቷን መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው። ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ወታደራዊ ባለስልጣናት በበኩላቸው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ወታደራዊ ዘመቻ የሚከፈትበትን ሁኔታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መምከር መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ መግለጫን የሰጡት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪክስ ቲለርሰን የሶሪያ ፕሬዚደንት ባሽር አላሳድ ሃገራቸውን ለመምራት ያላቸው ሚና አብቅቷል ሲሉ ገልጸዋል።
የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለ17 አመት በስልጣን የቆዩትን አላሳድ ለማስወገድ በሚካሄደው ዘመቻ ጠንካራ አጋርነቱን እንዲያሳይና ከአሜሪካ ጎን እንዲቆም ቲለርሰን መናገራቸውን አሶሼይትድ ፕሬስ እና CNN ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግበዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር (ፔንታገን) እና ኋይት ሃውስ የሶሪያ ቁልፍ ወታደራዊ ቅኝትን የሚያካሄዱ መሰረተ ልማቶች በክሩስ ሚሳይል የሚወድሙበትንን ሁኔታ እየመከሩ እንደሆነም ተገልጿል።
አሜሪካ ከሶሪያ ላይ ልትከፍት ያሰበችው ወታደራዊ ዕርምጃ በፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አስካለፈው ሳምንት ድረስ የነበረን አቋም ሙሉ ለሙሉ የቀየረ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል።
በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ኒክ ሃሊ ከቀናት በፊት ሃገራቸው የፕሬዚደንት ባሽር አላሳድ ከስልጣናቸው መወገድ ዋነኛ አማራጭ አድርጋ እንድትመለከት ገልጸው እንደነበር የዜና አውታሩ አውስቷል።
ይሁንና በተያዘው ሳምንት በፊት መጀመሪያ በአማጺያን ይዞታ ስር በምትገኘው የካን ሼኩን ከተማ ተፈጽሟል የተባለው የኬሚካል ጦር መሳሪያ አሜሪካ በሶሪያ ላይ ያላትን አቋም በሰዓታት ልዩነት እንድትቀይር ማድረጉን የፖለቲካ ተንታኝ አስታውቋል።
ማክሰኞ በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 100 አካባቢ የደረሰ ሲሆን፣ ከ20 የሚበልጡ ህጻናት መሆናቸው ተመልክቷል። የሶሪያ የጦር አውሮፕላኖች ከሰማይ ለቀውታል በተባለው በዚሁ የኬሚካል ንጥረ ነገር 350 አካባቢ ሰዎች ለህመም መዳረጋቸውን ሮይተርስ አርብ ዘግቧል።
በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የከተማዋ ነዋሪዎች መተንፈስ አቅቷቸው ሲቸገሩ አሳይተዋል። የሶሪያ ባለስልጣናት ድርጊቱ እንዳልፈጸሙ በመግለጽ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን ስምምነት መካሄድ ባለበት ሁኔታ ምርመራ እንዲያካሄድ ፈቃደኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ፕሬዚደንት ባሽር አላሳድ ከስልጣን እንዳይወርዱ ድጋፍ እያደረገ ያለችው ሩሲያ በበኩሏ የሶሪያ የጦር አውሮፕላኖች የአማጺያን ይዞታ ላይ ጥቃት በፈጸሙ ጊዜ ሲገለገሉበት የነበረ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ መርዘማ ጋዝ ጉዳት እንዲያደርስ ምክንያት ሆኗል ስትል ትገልጻለቸ።
ሩሲያ በሶሪያ ላይ ያለበት አቋም አሜሪካ ልትወስድ ባሰበችው ወታደራዊ ዘመቻ ከሃገሪቱ (አሜሪካ) ጋር ፍጥጫ ውስጥ ይከታታል ተብሎ ተሰግቷል።
በርካታ የምዕራባውያን ሃገራትም የሶሪያው ፕሬዚደንት ስልጣናቸው በሃይል ማብቃት እዳለበትና ሃሳብና ድጋፍ እያቀረቡ እንደሆነም ታውቋል። ይሁንና አሜሪካ በሶሪያ ላይ ልትወስድ ያሰበችው ወታደራዊ ዘመቻ አካባቢው ዘላቂ አለመረጋጋት ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።