(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 28/2010) ለአቤቱታ አዲስ አበባ የሚገኙት የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች በደህንነት መስሪያ ቤቱ በኩል ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው።
ከ150 በላይ የሚሆኑት የሀገር ሽማግሌዎቹ ከእንግዲህ የደህንነት ጥበቃ አይደረግላችሁም፣ እዚያው ሄዳችሁ ከአብዲ ዒሌ ጋር ታረቁ የሚል በህይወታቸው ላይ አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል የሚጠቁም ነው ሲሉ የሀገር ሽማግሌዎቹ ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል በሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ትዕዛዝ ከትላንት ምሽት ጀምሮ ወጣቶች እየታፈኑ በመታሰር ላይ መሆናቸውን የኢሳት ምንጮች ገለጸዋል።
እስካሁን 50 ወጣቶች ከጂጂጋ ታፍነው መወሰዳቸው ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ በፓርላም የተነሳው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሶማሌ ክልል እንደሚቀጥል አብዲ ዒሌ መናገራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከ2ወራት በላይ ሆኗቸዋል። በሶማሌ ክልል ህዝብ ላይ የሚደርሰው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየተባባሰ መጥቷል፡፡
ህዝብ ከፍተኛ ስቃይ ላይ ነው፣ ለዚህ ደግሞ ዋናው ችግር የሆነው የክልሉ ፕሬዝዳንት በመሆኑ መንግስት በአስቸኳይ ከስልጣን ያንሳልን የሚል አቤቱታ ይዘው አዲስ አበባ የገቡት ከ150 በላይ የሚሆኑት የሀገር ሽማግሌዎች የሚሰማቸው የሚያናግራቸው አጥተው በመንከራተት ላይ መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።
ሰሞኑን ወደ ቤተመንግስት ያመሩት የሃገር ሽማግሌዎቹ ከብዙ እንግልት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ለማግኘት ያደረጉት ጥረት በህወሃት ደህንነቶች በመታገዱ ሶስት ተወካዮች መርጠው ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ተደርገው ነበር።
በዛን ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ከሶስት ቀን በኋላ አግኝተው እንዲያናግሯቸው ቀጠሮ እንደተሰጣቸውና እኛም መዘገባችን ይታወሳል።
አሁን ግን የሀገር ሽማግሌዎቹ አዲስ አበባን ለቀው ወደ ሶማሌ ክልል እንዲመለሱና ከአብዲ ዒሌ ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ በህወሃት ደህንነት መስሪያ ቤት በኩል ከፍተኛ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑ ተሰምቷል።
ባለፈው ለተወሰኑ የህወሃት ጄነራሎች ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ሽማግሌዎቹን እንዲያስፈራሩ በአብዲ ዒሌ በኩል የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን መዘገባችን የሚታወስ ነው።
ሽማግሌዎቹ በህይወታችን ላይ አደጋ ሊደርስ ስለሚችል የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳያችንን ይወቅልን በማለታቸው ለጊዜው እፎይታን አግኝተው ነበር።
ይሁንና ከትላንት ጀምሮ የህወሃት የደህንነት መስሪያ ቤት ለሀገር ሽማግሌዎቹ የደህንነት ጥበቃ እንደማያደርግላቸው ማስታወቁን ተከትሎ የሀገር ሽማግሌዎቹ ህይወታችን አደጋ ላይ ወድቋል ሲሉ መናገራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የደህንነት መስሪያ ቤቱ በግልጽ እንደተናገረው ሄዳችሁ ከአብዲ ዒሌ ጋር ተስማምታችሁ ስሩ፣ የአብዲ ዒሌ በስልጣን መቆየት የሚጠቅመው እኛንም እናንተንም ነው ማለቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የሀገር ሽማግሌዎቹ በቶሎ ከአዲስ አበባ እንዲወጡ በደህንነት መስሪያ ቤቱ ግፊት እያደረገ ያለው የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ላለፉት 10 አመታት ተቀናቃኞቹን ከአዲስ አበባ እያሳፈነ በጄል ኦጋዴን በእስር እንዲማቅቁ በማድረግ የሚታወቅበትን ድርጊት በሽማግሌዎቹ ላይ ለመፈጸም ማቀዱም እየተነገረ ነው።
የሀገር ሽማግሌዎቹ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ጥበቃ ከተነሳ በአብዲ ዒሌ እጅ ላይ እንወድቃለን የሚል ስጋት ውስጥ እንዳሉም የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
ህወሀት የአብዲ ዒሌን በስልጣን መቆየት አጥብቆ እንደሚፈልገው ለሽማግሌዎቹ በመግለጽ ላይ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም አብዲ ዒሌ ተለጣፊ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን በመሰየም በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናትን እንዲገናኙ ውስጥ ውስጡን እየሰራበት መሆኑንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በሌላ በኩል ከትላንት ምሽት ጀምሮ በተለያዩ የሶማሌ ክልል ከተሞች አፈና በመከናወን ላይ መሆኑም ታውቋል።
በተለይም ወጣቶች እየታፈሱ ወደ ጄል ኦጋዴን ተወስደው መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ከትላንት ምሽት ጀምሮ ከጂጂጋ ብቻ 50 ወጣቶች መታፈናቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ክልላችን በሽብርተኞች እየተረበሸ ነው፣ ማንኛውንም የመከላከል ርምጃ እንወስዳለን በማለት መናገራቸው የተገለጸ ሲሆን ዛሬ የተነሳው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሶማሌ ክልል ግን እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ነው የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ የተቻለው።