የሶማሌ ክልል ሕዝብ በአቶ አብዲ ኢሌይ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ሢደርስበት የቆየውን ግፍና በደል ያለማሳለስ ሲታገሉና ሲያጋልጡ የቆዩት አክቲቪስት ሙስጠፋ ኡመር በርዕሰ ብሔርነት ክልሉን እንዲያስተዳድሩ ተመረጡ።

የሶማሌ ክልል ሕዝብ በአቶ አብዲ ኢሌይ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ሢደርስበት የቆየውን ግፍና በደል ያለማሳለስ ሲታገሉና ሲያጋልጡ የቆዩት አክቲቪስት ሙስጠፋ ኡመር በርዕሰ ብሔርነት ክልሉን እንዲያስተዳድሩ ተመረጡ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 17 ቀን 2010 ዓ/ም ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት ክፍል ውስጥ በጎረቤት ሀገራት እያገለገሉ የነበሩት የ 45 አመቱ አቶ ሙስጠፋ ኡመር ፣በአብዲ ኢሌይ ለስደት ከተዳረጉ የክልሉ ምሁራን መካከል አንዱ ናቸው።
ከክልሉ ከሥራ ተባረው ወደ አዲስ አበበ በመምጣት መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ ሥራ የጀመሩት አቶ ሙስጠፋ በፈላጭ ቆራጩ የአብዲ ኢሌይ አገዛዝ በክልሉ በወገኖቻቸው ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ግፎችን ከማጋለጥ ባለማቆማቸው ነው ወደ ጎረቤት ሀገር ለስደት የተዳረጉት።
ካሉበት የስደት ቦታ ሆነው የአክቲቪዝም ትግላቸውን በመቀጠላቸውም የ70 ዓመት አዛውንት አባታቸው በአብዲ ኢሌይ ታስረው ለእንግልት ከመዳረጋቸውም በላይ ወንድማቸው ኢንጂነር ፈይሰል ተገድሎባቸዋል።
እንደነ ሂዩማን ራይትስ ዎች በመሳሰሉ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ክስ የተመሰረተባቸውን እና በከፍተኛ ተደራራቢ ወንጀል የሚፈለጉትን አብዲ ኢሌይን በቅርቡ ከሥልጣን ያነሳው የክልሉ ምክር ቤት፣ በትናንትናው ዕለት አክቲቪስት ሙስጠፋን- አብዲ ኢሌይን ተክተው ክልሉን ይመሩ ዘንድ በርዕሰ ብሔርነት መርጧቸዋል።
አብዲ ኢሌይ ከሥልጣን ተነስተው በእስር ማቆያ በሚገኙበት ወቅት በአሳዳጃቸው ቦታ ላይ የተቀመጡት ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ የፊታችን ቅዳሜ ቃለ መሀላ በመፈጸም ሥልጣናቸውን በይፋ ተረክበው ሥራ ይጀምራሉ።
ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፋ እና አስተዳደራቸው በተለይ በህወኃት እየተዘወሩ የክልሉን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ለማጋጨት አቶ አብዲ ኢሌይ የዘረጉትን የልዩነትና የአምባገነንነት ሰንሰለት በመበጣጠስ እና ለሕዝቦች መቀራረብና የጋራ ጥቅም እግቶ በመሥራት ለተጀመረው ሀገራዊ አንድነት ጉልህ ሚና ይጫዎታሉ ተብሎ ይጠበቃል።