ግንቦት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢሳት እጅ በገባው የፕሬዚዳንቱን ሚስጢራዊ ንግግሮች በያዘው ፊልም ውስጥ እንደተመለከተው ፣ አቶ አብዲ የኢህአዴግ አጋር ድርጅት የሆነው የሶማሊ ህዝብ ዴሞክራሲ ፓርቲ ( ሶህዴፓ) አባላት በግዴታ የአባልነት መዋጮ እንዲከፍሉ መደረጋቸውን ተናግረዋል። ” መንግስት በአንድ በኩል ገንዘብ ይሰጣል በሌላ በኩል ደግሞ ገንዘብ ከፋዩዋ በግዴታ ከሰራተኞች እየቆረጠች ትወስዳለች” ብለዋል አቶ አብዲ።
አቶ አብዲ ድርጅታቸው ሶህዴፓ 40 ሺ አባላት እንዳሉት ተደርጎ ሪፖርት የሚቀርበውም ውሸት ነው ብለዋል። ” 40 ሺ አባላት ቢኖሩን ኑሮ ጸረ ሰላም ሀይሎች እንዴት ኖሩ?” በማለት የጠየቁት አቶ አብዲ፣ ያሉትም አባላት ቢሆኑ ገንዘባቸው በግዴታ በመንግስት የሚወሰድባቸው እንጅ በሙሉ ልብ የአባልነት መዋጮ የሚከፍሉ አይደሉም” ሲሉ አክለዋል።
እርሳቸው የድርጅት አባል የሚሉት በራሱ ፈቃድ መዋጮ የሚከፍል እንጅ መንግስት አስገድዶ የሚቆርጥበትን አለመሆኑን ግልጽ አድርገዋል።
ኢሳት በተከታታይ በለቀቃቸው የቪዲዮ ማስረጃዎች ፕሬዚዳንቱ “ ክልሉ እንዳደ ፣ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደደረ ተደርጎ በየጊዜው የሚቀርበው ሪፖርት ፍጹም ትክክል ያልሆነ ውሸት ነው። ከአሁን በፊት ይቀርቡ የነበሩ ሪፖርቶችም እንዲሁ ግምገማ ለማለፍ ተብሎ በውሸት ላይ ተመስርተው የተዘጋጁ መሆናቸውን ” መግለጻቸው ይታወሳል።
ፕሬዚዳንቱ ” ትግሬዎች፣ አማራ መልሶ ስልጣን እንዳይዝ ኦጋዴኖችን አስታጥቀው በጋራ አገሪቱን እንድንመራ ይፈልጉ ነበር፣ እኛ ግን እንደ አማራ ቆጥረናቸው ተኩስ ከፈትንባቸው፤ አማራ እና ትግሬ፣ አማራ እና ኦሮሞ መቼውንም አይታረቁም ፣ አይተባበሩም ስለዚህ የኦጋዴን ህዝብ ከትግሬ ጎን እንዲቆም፣ አማራ እና ትግሬን፣ አማራ እና ኦሮሞን አንድ አድርጎ አማራ እያለ መጥራቱን ያቁም” በማለት መናገራቸውም በሚስጢራዊ ቪዲዮው ውስጥ መጠቀሱ ይታወሳል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንትን ለማግኘት ሙከራ ብናደርግም ፕሬዚዳንቱ ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ጸሀፊያቸው ልታገናኝን አልቻለችም