የስዊድን መንግሥት አትሌት አበባ “ስዊድናዊ ነት ይላል

ሰኔ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጣሊያን ሮም በተደረገው ዳይመንድ ሊግ ኢትዮጵያን ወክላ በ1 500 ሜትር ውድድር ያሸነፈችው የአትሌት አበባ አረጋዊ የዜግነት ጉዳይ ውዝግብ አስነሳ።

አበባ ከሳምንታት በፊት ሮም ላይ በተደረገው ዳይመንድ ሊግ ውድድር፤ ገንዘቤ ዲባባንና ሌሎች የዓለማችንን

ታላላቅ አትሌቶች አስከትላ በመግባት አንጸባራቂ ድል መቀዳጀቷ ይታወሳል። አበባ፤በሮሙ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ  አገሯን ወክላ ከመሮጧ አኳያ፤ ኢትዮጵያ ለለንደኑ ኦሊምፒክ ከገንዘቤ ዲባባ በተጨማሪ በ 1 500ሜትር የምታሰልፈው አትሌት እንዳገኘች ሲነገር ቆይቷል::

ይሁንና የስዊድን መንግሥት አትሌት አበባ እ.ኤ.አ. በ2009 ዓመተ ምህረት ወደ ስዊድን አምርታ ዜግነት መጠየቋን  በማስታወስ፤ በጥያቄዋ መሰረት በቅርቡ ሰኔ 21 ቀን 2004 ዓ.ም. ዜጋ መሆኑዋን በይፋ ገልጿል::

የስዊድን መንግስት ለአበባ የዜግነት ጥያቄ ምላሽ የሰጠው፤ በቅርቡ በተካሄደው በሮሙ የዲያመንድ ሊግ- አሸናፊ በሆነች ማግስት ነው።

የስዊድን መንግስት ከዚህም በተጨማሪ አትሌት አበባ አረጋዊ ከሶስት ሳምንት በሁዋላ በሚጀመረው የለንደን ኦሊምፒክ ለስዊድን የምትሮጥ መሆኑዋን ጭምር በመጥቀስ፤ ጉዳዩን ለዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር  እንዳቀረበው – ለአትሌቷ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተናግረዋል::

የኢትዮጵያ ብሐራዊ አትሌቲክስ ቡድን አባል የሆነችው አበባ፤ በአሁኑ ጊዜ  ከቡድኑ አባላት ጋር በዝግጅት ላይ ትገኛለች።

በተፈጠረው ሁኔታ  ቅሬታ ያደረበት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፤ የስዊድን መንግሥት ለአለማቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን  ያቀረበው ጥያቄ አግባብነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስ፤ ፌዴሬሽኑ  አቤቱታውን ውድቅ እንዲያደርግ መጠየቁ ተሰምቷል።

አበባ ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያላትን ሐሳብ እንድትገልፅ በጠየቃት መሰረት፤ እ.ኤ.አ. በ2009 ዓ.ም  ወደ ስዊዲን አምርታ የዜግነት ጥያቄዋንም ለስዊድን መንግስት ማቅረቧን፤ ሆኖም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መኖርያ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር  ዜግነት እንዳልተሰጣት መናገሯን ሪፖርተር አመልክቷል::

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ  ከአገር አገር እየተንቀሳቀሰች ስትወዳደር የቆየችው፤ ኢትዮጵያዊት መሆኗን በሚያረጋግጠው የኢትዮጵያ ፓስፖርት መሆኑን ያብራራችው አትሌት አበባ፤ አሁን ውጤታማ መሆኑዋ ከተረጋገጠ በኋላ የዜግነት ጥያቄዋ መልስ ማግኘቱ ብዙም እንዳላስደሰታት ጠቅሳለች።

በመሆኑም፤በቀጣዩ የለንደን በኦሊምፒክም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች መሮጥ የምትፈልገው፤ ለኢትዮጵያ  መሆኑን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ለዓለማቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዳስገባች ተናግራለች::

በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ደንብ መሰረት፣ አንድ አትሌት በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ የአንድን አገር መለያ አድርጐ ከተወዳደረ በሁዋላ ዜግነት ቀይሮ ዜጋ ለሆነበት አገር መሮጥ የሚችለው፤ የግድ ሦስት ዓመት ከማንኛውም ውድድር ተገልሎ ከቆየ በኋላ ነው።

ከዚህ አኳያ ከሦስት ዓመት በፊት ሞሪሸስ ላይ በተካሄደው የ አፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በቅርቡ በሮም በተካሄደው ዳይመንድ ሊግ  አገሯን ወክላ የተወዳደረችው አትሌት አበባ፤ በለንደን ኦሎምፒክም ለኢትዮጵያ ለመሰለፍ ላላት ፍላጎት ህጉ እንደሚያግዛት የዘርፉ ባለሙያዎች አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide