መስከረም ፫(ሦስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ መንግስት በቀጣዩ ዓመት በሚጠናቀቀው የአምስት ዓመት ዕቅዱ በስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ
ለመገንባት ያቀደውን እንደማያሳካ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገለጹ።
በህወሃት ነባር ታጋይ አቶ አባይ ጸሐዬ የሚመራው የስኳር ኮርፖሬሽን ከነባርና ዕውቀትና ልምዱ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር ተግባብቶ መስራት ባለመቻሉ ብዙዎቹ ኮርፖሬሽኑንና በስሩ ከሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች ለቅቀዋል፡፡
ኮርፖሬሽን የገጠመውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ከውጪ አገር ባለሙያዎችን በመቅጠር ለማሟላት ያደረገው ጥረትም አመርቂ ውጤት እንዳላስገኘ ታውቋል፡፡ በቢሊየን የሚቆጠር ወጪ እየፈሰሰባቸው ያሉት 10 አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታና ሶስት ነባር ፋብሪካዎች የማስፋፊያ ስራ በማጠናቀቅ አገሪቱ በአማካይ በአሁኑ ሰዓት በዓመት የምታመርተውን 300ሺ ኩንታል ስኳር ወደ 2 ነጥብ 25 ሚሊየን ቶን ለማድረስ ያቀደች ቢሆንም ፕሮጀክቶቹን ሊመራ የሚችል የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል ካለመኖሩና የስራዎቹ ሒደትም ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጠ በመሆኑ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ አለመሳካቱ ብቻ ሳይሆን የፕሮጀክቶቹ የጥራት ሁኔታ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሶስቱ ፋብሪካዎች የማስፋፊያ ስራ የተጠናቀቀ ቢሆንም አዳዲሶቹ ፋብሪካዎች ግንባታ ግን በ2007 ዓ.ም ተጠናቀው ወደስራ መግባት እንደማይችሉ ተረጋግጦአል፡፡ ለዚህም የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 እና 3 ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ጨርሶ አለመጀመር በቂ ማሳያ መሆኑን የጠቀሰው ምንጫችን ግንባታቸው የተጀመሩት የኩራዝ አንድ፣የከሰም፣የጣና በለስ አንድና ሁለት ፋብሪካዎች ግንባታ አፈጻጸምም ቢሆን እጅግ መጓተት የሚታይበት ነው ብሎአል፡፡
የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ግንባታም በከፍተኛ ሙስና ረጅም ርቀት ሊሄድ ባለመቻሉ መስተጓጎሉንና ጉዳዩም በጸረ ሙስና ኮምሽን መያዙ ታውቋል፡፡
መንግስት የአምስት አመት የልማት መርሀግብሩን ለማሳካት የነደፈው እቅድ በሚቀጥለው አመት የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ብዙዎች እቅዱ እንደማይሳካ አስቀድመው የተነበዩት በተግባር እየታየ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። መንግስት ኢኮኖሚውን እስከ 2007 ኣም በ14 በመቶ የማሳደግ እቅድ ነበረው። አይኤም ኤፍ ባወጣው የቅርብ መረጃ የመንግስት 2005 እድገት ከ7 በመቶ አይበልጥም።