ኢሳት (ሚያዚያ 5 ፥ 2009)
የስነ ምግባር ጉድለት ተገኝቶባቸዋል የተባሉ አራት የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሃሙስ ወሰነ።
የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አራቱ ዳኞች ከፍተኛ የስነ-ምግባር ጉድለት ታይቶባቸዋል ሲል ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ለምክር ቤቱ ጥያቄን አቅርቦ እንደነበር ታውቋል።
ለመደበኛ ስብሰባ ተሰይሞ የነበረው ምክር ቤቱ ያለምንም ተቃውሞ አራቱ የፌዴራል ዳኞች ከስራቸው እንዲሰናበቱ የመጨረሻ ውሳኔ ማስተላለፏን የአገዛዙ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ውሂብ ማሞ እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች የነበሩት አቶ ዳግም መርጊያ፣ ወ/ት ግሩም አጎናፍር እና ወ/ት ብርሃኔ ኪዳኔ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉት ዳኞች መሆናቸው ታውቀዋል።
ወደ ስራ ገበታ አርፍዶ መምጣት፣ የክስ መዝገብን ማቆየት እንዲሁም በስራ ገበታ ላይ አለመገኘት በዳኞቹ ላይ የቀረበ ከፍተኛ የስነ ምግባር ችግር መሆኑን የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ለፓርላማው አስረድቷል።
የምክር ቤቱ አባላት በአብዛኛው ድምፅ አራቱ ዳኞች እንዲሰናበርቱ የወሰኑ ሲሆን፣ አንድ ተቃውሞ ብቻ መቅረቡ ተመልክቷል።
ባለፈው አመት በተመሳሳይ መልኩ ለህገ መንግስቱ ተገዢ አይደሉም የተባሉ አራት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ ይታወሳል።
ዳኞቹ በተለያዩ መድረኮች ህገ-መንግስቱ በሰብዓዊ መብት አከባበር ላይ ችግር እንዳለበትና የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እገዳ ተጥሎበታል ብለው በተለያዩ መድረኮች ተናግረዋል ተብለው ቅሬታ እንደቀረበባቸው አይዘነጋም።