ኢሳት (ሚያዚያ 6 ፥ 2009)
የዘንድሮው የእየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በአዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በመላ ሃገሪቱ በደማቅ ሃይማኖታዊ ስነስርዓት ተከበረ።
ይኸው የስቅለት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት በስግደት እንዲሁም በልዩ የጾም ስነ-ስርዓት ተከብሮ መዋሉን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
አርብ መከበር የጀመረው የስቅለት በዓል ምሽቱን በተለያዩ ቤተክርስቲያኖች በሚካሄዱ መንፈሳዊ ዝግጅቶች የሚቀጥል ሲሆን፣ እየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅን ለማዳን ሲል የተቀባላቸውን መከራዎች የሚያሳዩ መንፈሳዊ ትምህርቶች ይቀርባሉ።
ከነገ በስቲያ እሁድ የሚከበረውን የፋሲካን በአል በማስመልከትም የሃይማኖት አባቶች በዓሉ የሰላምና የተቸገሩ ሰዎችን በመደገፍ ታስቦ እንዲውል መልዕክትን አስተላልፈዋል። ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካና በተለያዩ የአለማችን ሃገራት የሆነ ኢትዮጵያውያን ከረቡዕ የስቅለት በዓል አከባባር ጀምሮ የፋሲካ በዓልን በቤተ-ክርስቲያኖች በሚካሄዱ መንፈሳዊ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ እያከበሩ እንደሚገኝ ታውቋል።
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የስቅለት በዓሉ በሩሲያ፣ ግሪክ፣ እንዲሁም በዚሁ በአሜሪካ በሚኖሩ የክርስቲያን ማህበረሰብ ዘንድ በመከበር ላይ ሲሆን፣ በእስራዔልና በተለያዩ የአውሮፓ ሃገራትም የበዓሉ ስነ-ስርዓት እየተካሄደ መሆኑን የአለም መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።