የስራ ማቆም አድማው ለ3ኛ ቀን ቀጥሎ ሲውል፣በቀብሪደሀር የህወኃት የጦር መኮንን በኦሮሚያ ፖሊስ እንደተገደሉ ተዘገበ።

የስራ ማቆም አድማው ለ3ኛ ቀን ቀጥሎ ሲውል፣በቀብሪደሀር የህወኃት የጦር መኮንን በኦሮሚያ ፖሊስ እንደተገደሉ ተዘገበ።
(ኢሳት ዜና የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ/ም) ለሶስት ቀናት የተጠራው የስራ ማቆም አድማ ዛሬም በተለይ በኦሮምያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ተግባራዊ ሆኗል። የፌደራል ፖሊሶችና የአጋዚ ወታደሮች በብዛት በመውጣት እንደተለመደው የንግድ ድርጅቶችን ሲያሽጉ ውለዋል። በድርጅቶቻቸው አቅራቢያ የተገኙ ነጋዴዎችም ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። አድማውን ያስተባብራሉ የተባሉ የመንግስት ሰራተኞች፣ የወረዳና የዞን አስተዳዳሪዎችም ተይዘው ታስረዋል።
በጅማ ከተማ ተቃውሞው ወደ አደባባይ ተቃውሞ ተለውጦ 2 ሰዎች በአጋዚ ወታደሮች መገደላቸው ታውቋል።
በሃረር ከተማ የምስራቅ እዝ ወታደሮች ነጋዴዎችን ሱቆቻቸውን እንዲከፍቱ ሲያስገድዱ ፣በሱቆቻቸው አካባቢ ያልተገኙ ነጋዴዎችን ድርጅቶች ሲያሽጉ ውለዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነጋዴዎችም መታሰራቸው ታውቋል። ድርጅቶቻቸውን በፍርሃት በከፈቱ ነጋዴዎች ላይ ህዝቡ እቃዎችን ያለመግዛት አድማ አድርጓል። ወኪሎቻችን ከየሥፍራው ያጠናቀሯቸው ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ ከሃረር ወደ አዲስ አበባ ሌሎችም ከተሞች የነበረው የህዝብ የትራንስፖርት አግልግሎት ዛሬም እንደተቋረጠ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ የተለያዩ የዞንና የወረዳ ባለስልጣናት በወታደራዊ አዛዦች ትዕዛዝ ታስረዋል። የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪን፣ የነቀምት ከተማ ከንቲባንና ምክትላቸውን፣ እንዲሁም የቄለም ወረዳ የፍትህ ቢሮ ሃላፊን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናት ታስረዋል።
የክልሉ ፖሊስ አዛዥ አዱኛ ደበላ ስልጣን መልቀቃቸው ይታወቃል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች በርካታ ወጣቶች ታፍሰው የታሰሩ ሲሆን፣ ትናንት 6 የቀይ መስቀል አምቡላንሶች በሽተኛ የሚያነሱ መስለው የታፈሱ ወጣቶችን ይዘው ድምጽ እያሰሙ ወደ ካራ( አየር ጤና) ይዘዋቸው መሄዳቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
በለገጣፎ ቄሮዎች ከአጋዚ ወታደሮች ጋር ተፋጠው መዋላቸውንና አጋዚዎች የንግድ ድርጅቶችን በጉልበት ለማስከፈት ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካለቸው እንደቀረ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በተለምዶ ኬንተሪ ከሚባለው አካባቢ ጀምሮ እስከ አለም ገና በሚገኙ ቦታዎች የተዘጉ የንግድ ድርጅቶችን የአጋዚ ወታደሮች በጉልበት ማስከፈት ሲጀምሩ፣ አጋዚዎች ዞር ማለታቸውን ሲያዩ ቄሮዎች በፍጥነት ሄደው ነጋዴዎችን “ በሉ ዝጉ” በማለት ሲያዘጉ ውለዋል። ከሰዓሊተምህረት እስከ ለገጣፎ ባሉት አካባቢዎች ላለፉት 3 ቀናት መብራት እንዲጠፋ መደረጉንም፣ የአካባቢዎች ነዋሪዎች በሃዘን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የኦሮምያ ክልል ፖሊስ አባላት ለአንድ ሳምንት ያክል የደንብ ልብሳቸውን ሳይቀይሩ በስራ መጨናነቃቸውን ተናግረዋል። ስርዓቱ የህዝቡን ችግር ለመፍታት አለመቻሉን የሚገልጹት ፖሊሶች፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማይደግፉና ግዳጃቸውን የማይወጡ ከሆነ ከስራ እንደሚባረሩና እስር እንደሚጠብቃቸው እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጉሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሃገሪቱ የተፈጠረው ተቃውሞ የቀለም አብዮት መልክ እየያዘና በግልጽ ስልጣን የመፈለግ አዝማሚያ እየታየበት መምጣቱን ተናግረዋል። አቶ ሲራጅ መቼም ቢሆን በነውጥ፣ በአቋራጭና በውጭ ሃይሎች ተፅዕኖ የሚለወጥ መንግስት አይኖርም ብለዋል።
ባለስልጣኑ አዋጁ ከታወጀ በሁዋላ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ በተቋማትና ፋብሪካዎች ላይ ጉዳት መድረሱን በመግለጽ፣ አዋጁ አለመስራቱን አምነዋል።
ኮማንድ ፖስቱ ከታወጀ ወዲህ እስካሁን ድረስ 17 ወታደሮች ላይ ጉዳት መድረሱን፣ የመሳሪያ ነጠቃ መፈጸሙን፣ 4 መኪኖች መቃጠላቸውንና 10 መኪኖች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው አቶ ሲራጅ ተናግረዋል።
በተቃውሞው ተሳትፈዋል የተባሉትን ማሰር መጀመሩንም አቶ ሲራጅ ተናግረዋል።
አቶ ሲራጅ አገዛዙ ከፍተኛ ፈተና ውስጥ መግባቱን በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል። የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡም ከፍተኛ ችግር መፈጠሩን ባለስልጣኑ አምነዋል።
በሌላ በኩል በሶማሌ ክልል በቀብሪደሀር ከተማ አንድ ከፍተኛ የህወኃት ጦር አዛዥ በኦሮሚያ ፖሊስ መገደላቸውን ኦጋዴን ኦንላይን ዘግቧል።
ይህን ተከትሎ ከተማዋ ብዛት ባላቸው የአጋዚ ሠራዊት ሥር የወደቀች ሲሆን፤ አካባቢው በከፍተኛ ውጥረትና ትርምስ ተሞልቷል።
ከሁለት ቀናት በፊት ምሽት ላይ በአምቦ በአጋዚ ታጣቂዎችና በኦሮሚያ ፖሊስ መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደተደረገ መዘገቡ ይታወሳል።