መስከረም ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ለ5ኛ ቀን ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ዛሬም የንግድ ድርጅቶችን ለማስከፈት ጥረት ሲያድረጉ ቢውሉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። እሁድ ማንኛውም የንግድ ድርጅት ይከፈታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የንግዱ ማህበረሰብ ህዝባዊ እንቢተኝነቱን በመምራትና በማስተባበር እያደረገ ያለው ድጋፍ አስገራሚ መሆኑን ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ሰዎች ገልጸዋል።
በጎንደር፣ ባህርዳር፣ አዲስ ዘመን፣ ጅጋ እና ሌሎችም ከተሞች በንግዱ ማህበረሰብ ላይ እስራት፣ የንግድ ፈቃድ መሰረዝና ቅጣት የመሳሰሉት መሳፈራሪያዎች ቢደረጉበትም ፣ ነጋዴዎች ለማስፈራሪያው ሳይንበረከኩ አድማውን በአንድነት ተግባራዊ አድርገዋል። ከገዢው ፓርቲ ጋር የወገኑ አንዳንድ ድርጅቶች ስራ ለመጀመር ሙከራ ቢያድረጉም በህዝቡ በመወገዛቸው በቂ ደንበኞችን ማግኘት አለመቻላቸውን የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ገልጸዋል።
ነጋዴዎች የቤት ኪራይ ወጪያቸውን በጋራ እየተባበሩ በመሸፈን እንዲሁም ሳምንታዊ እቁብ የሚጥሉትን ሳይቀር እየዘለሉ አድማውን ያደረጉ ሲሆን፣ በተለይ በበባህር ዳር ለተወሰኑ ነጋዴዎች በስማቸው እየተጻፈ ለሰባት ቀን እገዳ እንደተጣለባቸው በመታወቁ ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ የተጣለው እገዳ እስካልተነሳ ድረስ ሱቃቸውን ላለመክፈት መነጋገራቸው ታውቋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ነጋዴውን ከፋፍሎ ለመምታት በተወሰኑት ላይ እግድ ሲጥል በተወሰኑት ላይ ደግሞ እግድ አልጣለም። ድርጊቱ ሆን ተብሎ ነጋዴዎችን ለመከፋፈል የተቀነባበረ በመሆኑ ሁሉም ነጋዴዎች በአንድነት ከታገደባቸው ነጋዴዎች ጎን በመቆም አንድነታቸውን መሳየት አለባቸው ሲሉ የነጋዴዎች ወኪሎች ምክራቸውን ይለግሳሉ።
በጎንደር ደግሞ 5 የባጅጀና 3 የታክሲ ማህበር መሪዎች6ኛ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ ሲሆን፣ ከ30 በላይ የሚሆኑት የማህበሩ አመራሮች እየታደኑ ነው። ከእዚሁ ጋር በተያያዘ የጎንደርን ህዝባዊ ንቅናቄ ሲመሩ ነበር የተባሉ ሰዎች ጎንደር ፍርድ ቤት ከቀረቡ በሁዋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በፌደራል ደረጃ መታየት ስላለበት ወደ አዲስ አበባ መሄድ አለባቸው ብሎ በመወሰኑ የተወሰኑ ሰዎች ወደ አዲስ አበባ ሊሄዱ መሆኑ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ገዢው ፓርቲ የመስቀል በአልን ለማደናቀፍ የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ መዘጋጀቱን መረጃ እንደደረሳቸው የገለጹት የሃይማኖት አባቶች፣ ዛሬ ከወጣቶች ጋር ባደረጉት ስብሰባ በአሉ በመስቀል አደባባይ እንዳይከበርና በየቤተክርስቲያኑ ብቻ በዝምታና በጸሎት እንዲከበር ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በቅርብ ጊዜ የጎንደር ከተማ ታሪክ የመስቀል በአል ከመስቀል አደባባይ ውጭ ሲከበር ይህ የመጀመሪያ ይሆናል። አብዛኞቹ አማራ ክልል ከተሞች በወታደራዊ ቁጥጥር ስር በመዋላቸው በሌሎችም አካባቢዎች የመስቀል በአል በአደባባይ የመከበሩ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል።
በአዲስ አበባ በአሉ በምን አይነት ሁኔታ እንደሚከበር ግልጽ አይደለም።