(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 16/2010) በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የስራ ማቆም አድማና ተቃውሞ ሲደረግ መዋሉ ተሰማ።
በባህርዳር መውጪያና መግቢያ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ጥብቅ ፍተሻ በመደረግ ላይ መሆኑ ታወቋል።
በእንጅባራ ውጥረት መኖሩ እየተነገረ ነው።
በአምቦ መስመር ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ከቤት ውስጥ ያለመውጣት አድማ በመደረግ ላይ ነው።
በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አንዳንድ ከተሞች ተመሳሳይ አድማ ተጀምሯል።
በኢሉባቡር ጎሬና በወለጋ ሆሮ ጉዱሩ ሻምቡ ተቃውሞ በመካሄድ ላይ ነው።
አምቦ መስመር ዛሬም ጭር ማለቱ ቀጥሏል። ገበያዎች አልቆሙም። ሰዉ ከቤት አልወጣም።
ጊንጪ፣ ግንደበረት፣ጉደርና በርከት ያሉ የገጠር መንደሮች ድረስ የዘለቀውና አራተኛ ቀኑን ያስቆጠረው አድማ ዓላማው ለህወሃት መንግስት አልገዛም ባይነትን ማሳየት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በአምቦ እየተካሄደ ባለው በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ከጥቂት ተሽከርካሪዎች በቀር ጎዳናዎች ከእንቅስቃሴ ውጭ መሆናቸው ተመልክቷል።
ትምህር ቤቶች ዝግ ናቸው። የንግድ ቦታዎች አገልግሎት አቁመዋል።
ይህ ዓይነቱ የስራ ማቆምና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ አዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎችም በመካሄድ ላይ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያስረዳል።
በሱሉልታ ታክሲዎች ስራ ያቆሙ መሆናቸውን ዛሬ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የስራ ቦታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ የሱሉልታ ነዋሪዎች በታክሲዎች አድማ ምክንያት ወደስራ ገበታቸው መሄድ እንዳልቻሉ ታውቋል።
የታክሲዎቹን አድማ ሌሎችም ሊቀላቀሉት ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አድማው እስከ ጫንጮ የዘለቀ ሲሆን ወጣቶች አደባባይ በመውጣት የህወሀትን መንግስት ሲያውግዙ መዋላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
እዚያው በአዲስ አበባ ዙሪያ አለልቱ በተባለች ከተማም ነዋሪው የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጉ ታውቋል።
በዚህ ተቃውሞ ‘’ወያኔ አይገዛንም’’’ መሪዎቻችን ይፈቱ’’ የተሰኙ መልዕክቶች በነዋሪው መተላለፋቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል በኢሉባቡር ጎሬ ህዝባዊ ተቃውሞ ተካሂዷል።
በጎሬ ዋና አደባባይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች በጨለንቆው ጭፍጨፋ ለተገደሉት ሀዘናቸውን፣ ለህወሀት መንግስት ደግሞ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
በወለጋ ሆሮጉዱሩ ሻምቡ በተደረገው ተቃውሞ ህዝቡ በህወሀት መንግስት መገዛት አንፈልግም፣ በአስቸኳይ ስልጣን ይልቀቅ የሚል ጥያቄ በማንሳት በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ሰልፍ ማድረጉ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባህርዳር ከቅዳሜ ጀምሮ መግቢያዋና መውጫዋ በጥብቅ ፍተሻ ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በተለይ በህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ላይ ተሳፋሪን በሙሉ በማስወረድ ፍተሻ እየተደረገ ሲሆን ጸረ ሰላም ሀይሎች ሰርገው ገብተዋል የሚል ስጋት መኖሩን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ወደ አዲስ አበባ መውጪያ ድብናቄ መድሃኒዓለም ቤተክርስቲያን አጠገብ የተተከለው ኬላ ዋና የፍተሻው ቦታ እንደሆነ ታውቋል።
ወደ ጎንደር መውጫ አባይ ማዶ፣ ወደ አዴት መንገድ ሰባጣሚት ቀበሌ ላይ ጥብቅ ፍተሻ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚጠቀሱ ናቸው።
በተያያዘ ዜና በእንጅባራ ህዝባዊ ተቃውሞ ይነሳል የሚል ስጋት እንዳለ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በተለይም በእንጅባራ ዩኒቨርስቲ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት መሰማራቱ ያስቆጣቸው ነዋሪዎች በአስቸኳይ ጦሩ እንዲወጣ በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን የኢሳት ወኪሎች ከስፍራው ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።