የስራ ማቆምና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማው እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 13/2010)

በአማራ ክልል የተጠራው የስራ ማቆምና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉ ታወቀ።

በመጀመሪያው ቀን አድማ ያልተሳተፉ ከተሞች ዛሬ ተቀላቅለዋል።

ጎንደር በተጠናከረ መልኩ የአድማውን እንቅስቃሴ እያደረገች ነው።

በባህርዳር በአብዛኛው ሱቆችና መደብሮች ተዘግተዋል።

ባህርዳር ከትላንት ይልቅ ዛሬ አድማ ላይ ጠንክራ ብቅ ብላለች።

በአገዛዙ ታጣቂዎች ወከባ ከፍተው የነበሩ አንዳንድ የንግድ ቦታዎች ዛሬ ከረፋድ ጀምሮ አድማውን መቀላቀላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በተለይ በቀበሌ 4 ቡቲክ ተራ፣ ቀበሌ 12 ሜላት መስመር የሚገኙ የንግድ ቦታዎች ዛሬ ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል።

የአገዛዙ ካድሬዎች ከታጣቂዎች ጋር ሆነው ለማስከፈት እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም የአንዳቸውም የንግድ መደብር እንዳልተከፈተ ለማወቅ ተችሏል።

ትላንት በባህርዳር ፓፒረስ በሚባል ሆቴል አቅራቢያ በሚገኝ የደህንነትና ፖሊስ መሰባሰቢያ ቦታ አካባቢ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙም ታውቋል።

በዚሁ ጥቃት የደህንነት ክፍሉ ተሽከርካሪ መውደሙ ተገልጿል።

አደጋውን ያደረሰው አካል አልታወቀም። በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።

የአድማውን ጥሪ ባለመቀበል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 6 ተሽከርካሪዎችም ጥቃት እንደተፈጸመባቸው መረጃዎች አመልክተዋል።

ጎንደር ዛሬ ሙሉ በሙሉ ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆና ውላለች።

ሆቴሎች፣ የንግድ መደብሮችና የመንግስት ተቋማት፣ በሙሉ ተዘግተው የዋሉ ሲሆን የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴም እንዳልነበረ የደረሰን መረጃ ላይ ተመልክቷል።

በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ መፈታት ደስታዋን እየገለጸች ያለችው ጎንደር ትላንት የጀመረችውን አድማም አጠናክራ መቀጠሏ ታውቋል።

ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ኮሎኔል ደመቀ መኖሪያ ቤት ለመሄድ በረጅም ሰልፍ ሆኖ ሲጠባበቅ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።

ጎንደር የተመታው አድማ በዙሪያ ያሉ ወረዳዎችንም ከእንቅስቃሴ ውጭ ማደረጉን መረጃዎች አመልክተዋል።

አምባጊዮርጊስ፣ ደባርቅ፣ ዳባትና ገደብዬ የተባሉ ከተሞች አድማ ተመቶባቸዋል።

በደባርቅ የአገዛዙ ታጣቂዎች የሃይል ርምጃ ለመውሰድ ሲንቀሳቀሱ ከህዝቡ ጋር መጋጨታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በደብረታቦር፣ ጋይንት፣ ማክሰኝት፣ ወገራም እንዲሁ አድማ መመታቱ ታውቋል።

ከጎንደር ወደ ባህርዳር በሚወስደው መንገድ ሀሙሲት በተሰኘችው ከተማ ላይ ትላንት በአገዛዙ ታጣቂዎች ሁለት ወጣቶች ተገድለዋል።

መንገድ ሲዘጉ ነበር በሚል በታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት በተገደሉት ወጣቶች የተቆጣው የአካባቢው ነዋሪ ተቃውሞ እያሰማ መሆኑ ታውቋል።

ዘግይቶ በደረሰን ዜናም ከጎንደር ህዝባዊ እምቢተኝነት ጋር በተያያዘ በሽብርተኝነት ተከሳ ከፍተኛ ስቃይ ሲፈጸምባት የነበረችው ወጣት ንግስት ይርጋ ዛሬ መፈታትቷን ለማወቅ ተችሏል።