(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 22/2010)
በሕገመንግስታቸው ፕሬዝዳንታዊ የስልጣን ገደብ በሌላቸው ሃገራት ግጭቶች እንደሚባባሱና የተረጋጋ አስተዳደር እንደሌለ አንድ ጥናት አመለከተ።
አፍሪካ የስትራቴጂክ ጥናት ማዕከል የተባለ ተቋም ባካሄደው ጥናት እንደተገለጸው በሕገመንግስት ፕሬዝዳንታዊ የስልጣን ገደብ ከሌላቸው ሀገራት ብዙዎቹ በአፍሪካ ቀንድና በማዕከላዊ አፍሪካ የሚገኙ ናቸው።
አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ፕሬዝዳንቶች ደግሞ ሕገመንግስት በማሻሻል ገደቡን እንደሚጥሱም በጥናቱ ተመልክቷል።
በአፍሪካ ሃገራት የመሪዎችን ስልጣን ሕገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ለመገደብ ሙከራ ያደረጉ መሪዎች ቢኖሩም ሁኔታው የተዘበራረቀ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል።
በጥናቱ እንደተመለከተው 5 የአፍሪካ ሃገራት በሕገ መንግስታቸው የፕሬዝዳንትን ስልጣን ከገደቡ በኋላ እንደገና ማሻሻያ በማድረግ የራሳቸውን ሕግ ጥሰዋል።
እናም በአሁኑ ሁኔታ 18 የአፍሪካ ሀገራት በሕገመንግስታቸው የስልጣን ገደብ የሚባል ነገር እንደሌላቸው ጥናቱ አመልክቷል።
በሌላ በኩል 21 የአፍሪካ ሀገራት ፕሬዝዳንታዊ የስልጣን ገደብ በሕገመንግስታቸው ማስፈራቸው ነው የተገለጸው።
በቅርቡም ተጨማሪ 15 ሀገራት ተመሳሳይ ርምጃ ወስደዋል።
እናም በሕገመንግስት ፕሬዝዳንታዊ የስልጣን ገደብ መኖር አዎንታዊ ሚና ቢኖረውም ብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገራት ግን ያስቀመጡትን ገደብ እንደሚጥሱ አሕጉራዊው የስትራቴጂካዊ የጥናት ማዕከል አስታውቋል።
ከነዚህም መካከል በማዕከላዊ አፍሪካ ከ10ሩ 8ቱ ሕገመንግስቱን ጥሰው የስልጣን ዘመናቸውን አራዝመዋል ብሏል ጥናቱ።
በጥናቱ እንደተመለከተው አብዛኞቹ አምባገነን መሪዎች በአማካኝ ከ22 አመታት በላይ በስልጣን ላይ ይቆያሉ።
በዚህ በኩል በተለይ የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ተጠቃሽ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
የሕገመንግስት የስልጣን ገደብ ያስቀመጠላቸውና ረጅም ጊዜ በፕሬዝዳንትነት በሚቆዩባቸው ሀገራት ታዲያ ግጭቶች እንደሚባባሱና የተረጋጋ አስተዳደር አለመኖሩን ጥናቱ አመልክቷል።
በሕገመንግስታቸው የመሪዎች የስልጣን ገደብ ሙሉ በሙሉ የለም ከተባሉ ሃገራትም ኢትዮጵያ፣ኤርትራ፣ጋምቢያ፣ሌሴቶ፣ሞሮኮ፣ሶማሊያ፣ደቡብ ሱዳንና ስዋዚላንድ ተጠቃሽ ናቸው።
ከአፍሪካ ሃገራት በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመሩ ሁለት ሃገራት ሲሆኑ እነሱም ኢትዮጵያ እና ሞሪሼየስ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ሕገመንግስት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመን ገደብ እንደሌለውም ይታወቃል።
ገደቡን የጣሱት ደግሞ ግብጽ፣ዩጋንዳ፣ሱዳንን ጨምሮ 14 የአፍሪካ ሃገራት መሆናቸው ነው የተነገረው።
በሕገመንግስት የስልጣን ገደብ አስቀምጠው ለማሻሻል ሙከራ አድርገው ያልቻሉት ደግሞ ዛምቢያ፣ማላዊ፣ናይጄሪያ፣ኒጀር፣ሴኔጋልና ቦርኪናፋሶ ናቸው።
በቃላቸው መሰረት በሕገመንግስት የተቀመጠን ቀነ ገደብ አክብረው ስልጣን የለቀቁባቸው ሃገራትም በጥናቱ መሰረት ታንዛኒያ፣ጋና፣ደቡብ አፍሪካ፣ቦትስዋናና ሌሎች 15 ሀገራት ብቻ መሆናቸውን ጠቅሷል።