የሲ አይ ኤ ዳይሬክተር ከሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት ጋር በሚስጥር መገናኘታቸው ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 10/2010)  የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲ አይ ኤ ዳይሬክተር ማይክ ፖምፒዮ ከሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት ጋር በሚስጥር መገናኘታቸው ታወቀ።

ግንኙነቱ እውነት መሆኑን ያረጋገጡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መልካም ግንኙነት ተመስርቷል ሲሉ በቲውተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የ41ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባለቤትና የ43ኛው ፕሬዝዳንት እናት ባርባራ ቡሽ በ92 አመታቸው ከዚህ አለም ተለይተዋል።

በቅርቡ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ታጭተው የሴኔቱን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት የሲ አይ ኤው ዳይሬክተር ማይክ ፖምፒዮ ወደ ሰሜክ ኮሪያ የሚስጥር ጉዞ ያደረጉት በዚህ ወር መጀመሪያ እንደሆነም ታውቋል።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ማይክ ፖምፒዮ ወደ ሰሜን ኮሪያ ያቀኑት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በታጩ ማግስት ነው።

ሬክስ ቴለርሰንን በመተካት አዲሱን የሃላፊነት ስፍራ ከመያዛቸው በፊት ወደ ሩቅ ምስራቅ ሰሜን ኮሪያ ያቀኑት የሲ አይ ኤው ዳይሬክተር ማይክ ፖምፒዮ በሁለቱ ሃገራት መሪዎች መካከል ቀጥተኛ ንግግር በሚካሄድበት ሁኔታ ላይ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር መስማማታቸውም ተመልክቷል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሚስጥራዊ ጉብኝቱን በተመለከተ በቲውተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት እጅግ ከፍተኛ በሆነ ልኡክ ደረጃ በሚደረገው ቀጥተኛ ውይይት  አሜሪካ እንደምትሳተፍ አረጋግጠዋል።

የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስ ይህ ማለት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ቀጥተኛ ውይይት ማለት አይደለም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሆኖም መገናኛ ብዙሃን ቀጥተኛ ውይይቱ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር እንደሚሆን እየዘገቡ ይገኛሉ።

“ማይክ ፖምፒዮ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ባለፈው ሳምንት በሰሜን ኮሪያ ተወያይተዋል።ውይይቱ በመግባባት ላይ የተመሰረተና መልካም ግንኙነት የተፈጠረበት ነው።በውይይቱ ዝርዝር ውጤት ላይ እየሰራንበት ነው” በማለት ትራምፕ በቲውተር ገጻቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ትራምፕ ሲቀጥሉም ”አለማችንን ከኒዩክለር ነጻ ማድረግ ለዓለም ትልቅ ጉዳይ ነው።ለሰሜን ኮሪያም ጭምር”በማለት የግንኙነቱን ፋይዳም አብራርተዋል።

በሌላ ዜና የአሜሪካ 41ኛ ፕሬዝዳንት ባለቤትና ቀዳማዊት እመቤት የነበሩት እንዲሁም የ43ኛው ፕሬዝዳንት እናት ባርባራ ቡሽ በ92 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1988 እስከ 1993 በጆርጅ ቡሽ (ትልቁ) የመሪነት ዘመን ቀዳማዊት እመቤት የነበሩት በፖለቲካዊ ጉዳዮች በንቃት በመሳተፍ የሚጠቀሱት ባርባራ ቡሽ ልጃቸው ጆርጅ ቡሽም 43ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲመረጡም በምርጫው ዘመቻ ወቅት ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል።

በ92 አመታቸው በህመም ሕይወታቸው ያለፈው ባርባራ ቡሽ ሌላኛው ልጃቸው ጄ ቡሽም ለፕሬዝዳንትነት የተወዳደረ ቢሆንም አልተሳካለትም።

በአሜሪካ ታሪክ ባለቤታቸውም ልጃቸውም ፕሬዝዳንት የሆኑላቸው የመጀመሪያዋ እንስት አቢጌል  አዳምስ ሲሆኑ ባርባራ ቡሽ 2ኛ ሆነው ተመዝግበዋል።

አቤጌል አዳምስ የ2ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆን አዳምስ ባለቤትና የ6ኛው ፕሬዝዳንት ጆን ኪዊንስ አዳምስ እናት ነበሩ።