ግንቦት ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅርቡ ከኢትዮጵያ መሬት ተቆርሶ ለሱዳን ለመስጠት ከ12 ዓመታት በፊት የተጀመረው ድርድር ተግባራዊነት እውን ሊሆን ጫፍ መድረሱን ተከትሎ የሱዳን የመገናኛ ብዙሃን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እየዘገቡት ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ገበሬዎቹ የሚሰጠን መሬት ትንሽ ነው በማለት እያማረሩ መሆኑን የሱዳን ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው።
በገዳሪፍ አካባቢ የሚኖሩ የሱዳን ገበሬዎች በቅርቡ የግዛቱ አስተዳዳሪ የሆኑት ሚርጋኒ ሳልህ ሁሉም የእርሻ መሬቶች በቅርቡ ለሱዳን አርሶአደሮች ይሰጣሉ፣ ይህንኑ ተግባራዊ የማድረግ እንቅስቃሴም ተጀምሯል በማለት የተናገሩትን ገበሬዎች ሃሰት ነው ብለዋል።
በርካታ አርሶአደሮች ባወጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያኖች ከ2 ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ መሬት ይዘው እያረሱ ነው ማለታቸውን ደባንጋ ሬዲዮ ዘግቧል። የገዳሪፍ አስተዳዳሪ ተደራድሮ የሚያስመልሰው መሬት ከ60 ካሬ ኪሎሜትር የማይበልጥ መሆኑ ገበሬዎች ተናግረዋል።
የሱዳን ፖለቲከኞች በመሬቱ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው እየተነጋገሩ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በኩል ጉዳዩን በድብቅ ለማስፈጸም ሙከራ እየተደረገ ነው።
በሁለቱ ድንበሮች አካባቢ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደና መሬት የማስረከቡ እንቅስቃሴ የተጀመረ መሆኑን ኢሳት ለማረጋገጥ ቢችልም፣ ለሱዳን የሚሰጠውን የመሬት ስፋት ልክ በትክክል ማወቅ አልቻለም።