የሱዳን አማፅያን ጥቃት ሊፈጽምባቸው የሄደን የመንግስት የጦር አውሮፕላን መተው መጣላቸውን ገለፁ

ህዳር ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የሱዳን ህዝቦች የነፃነት ንቅናቄ እንዳለው፤ አማጽያኑ የመንግስትን  አንቶኖቭ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን  በደቡብ ኮርዶፋ ግዛት ጃው በተባለ አካባቢ ከአፈር ጋር ቀላቅለውታል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የአልበሽር አስተዳደር እስካሁን የሰጠው አስተያዬት የለም።

በ አማጽያኑ እና በመንግስት  ሠራዊት መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ ከደቡባዊ ኮርዶቻና ከጥቁር አባይ ግዛቶች ብቻ በ አስር ሽዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ቀያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ቢቢሲ አመልክቷል።

የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ወይም በ እንግሊዥኛው ምህፃረ-ቃል የ ኤስ.ፒ.ኤል.ኤም ቃል አቀባይ  አርኑ ንግቱሉ  ሎዲ ለ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደነገሩት  የመንግስት ቦምብ ጣይ አውሮፕላን  በ አማጽያኑ ተመትቶ የወደቀው ባለፈው ረቡዕ ነው።

<<አማጽያኑ  አውሮፕላኑን  ከመቱት በሁዋላ ክንፎቹ በ እሳት ሲቃጠል አይተውታል። ከዚያም  ወደ ታች ተምዘግዝጎ  የሁለቱ ሱዳኖች ድንበር በሆነችው በጃው አካባቢ ተከስክሷል>>ብለዋል-ቃል አቀባዩ።

ቢቢሱ እንዳለው አማጽያኑ በመንግስት የጦር አውሮፕላን ላይ ፈጽመነዋል ያሉት ጥቃት በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም። ምክንያት? ከአካባቢው  መረጃ ለማግኘት የማይቻል በመሆኑ።