(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 26/2010)
የሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ተይዘው የነበሩ 177 ሰዎችን ማስለቀቃቸውን አስታወቁ።
ከህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ እጅ እንዲወጡ ተደርገዋል የተባሉት እነዚህ ሰዎች ከካርቱም በስተምስራቅ ምስራቅ ናይል በተባለው ስፍራ ለ21 ያህል ቀናት ተይዘው መቆየታቸውንም ባለስልጣናቱ ገልጸዋል ሲል የቻይናው የዜና ምንጭ ሽንዋ በዘገባው አስፍሯል።
የካርቱም የፖሊስ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ኢብራሒም አብዱል ራሂም እንዳሉት በከፍተኛ ቅንጅት በተካሄደው አሰሳ ህገወጥ አዘዋዋሪዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።
ስደተኞቹንም ማዳን ተችሏል ሲሉ አክለዋል።
ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የፖሊስና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ክፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን የፖሊስ አዛዡ ገልጸዋል።
የፖሊስ አዛዡ እንደሚሉትም ሀገራቸው ሱዳን በቀጠናው ያለውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ለማስቆም ለምታደርገው ጥረት በዙሪያዋ ያሉት የኢትዮጵያ፣ኤርትራ፣ጅቡቲና ኬንያን ድጋፍ ትሻለች።
ከአውሮፓ ሃገራትም ስፔን፣ጣሊያን፣ብሪታኒያና ፈረንሳይም ድጋፍ እንዲያደርጉላት ትፈልጋለች ብለዋል።
ሱዳን በህገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ለሚጓዙ ሰዎች እንደመሸጋገሪያ ማገልገሏ ደግሞ ችግሩ በስፋት እንዲታይባት አድርጓታል ይላል ዘገባው።