ጥር ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር ለአልጀዚራ እንደተናገሩት “ኢትዮጵያ አልፋሽጋ የሚባለው ግዛት የሱዳን መሆኑን እንደምትቀበልና ለማስረክብ መቁረጧን” ተናገሩ።
ለሱዳን ይሰጣል የተባለው መሬት 250 ካሬ ኪሎሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ለም የሆነ መሬትና በርካታ የውሃ ተፋሰሶች ያሉት ነው።
የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያ አርሶአደሮች መሬቱን ሰጥቷቸው ሲያርሱት ነበር ያሉት ባለስልጣኑ፣በዚህ አመት ውስጥ መሬቱን ኢትዮጵያ ለሱዳን ልታስረክብ መሆኑን ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ንግግር፣ አቶ ሃይልማርያም ደሳለኝ በቅርቡ የሰጡትን መግለጫ የሚያጠናክር ነው። አቶ ሃይለማርያም የኢትዮጵያ ባለሃብቶችና አርሶአደሮች ወደ ሱዳን ገብተው እያረሱ መሆኑንና የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳንን መንግስት ለምኖ እስካሁን በቦታው ላይ እንዲቆዩ ማድረጉን ተናግረው ነበር።
የሱዳን መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጡት መግለጫ ከኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር ጋር መመሳሰሉ የተጠቀሰው መሬት ለሱዳን እንደሚሰጥ ማረጋገጫ ነው። በድንበሩ አካባቢ ያሉ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች ግን መሬቱ የኢትዮጵያ መሆኑን ይናገራሉ።
የኢህአዴግ መንግስት መሬቱ የሱዳን መሆኑን አምኖ ከተቀበለ ቀሪው ነገር አለማቀፋዊ ህጋዊነትን ማላበስ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ ሁለቱም መንግስታት ተስማምተው ስምምነታቸው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከገለጡ፣ መሬቱን መልሶ ለማግኘት ጉዳዩን ውስብስብ ሊያደርገው ይችላል።
የመንግስት ቃለአቀባይ ጌታቸው ረዳ እና ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የድንበር ጉዳይን ለማየት የተቋቋመ ኮሚቴ እንደሌለ፣ መሬት ለመስጠት ምንም ዝግጅት እንደሌለ ሲገልጹ ቆይተዋል። ይሁን እንጅ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሪዎች ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። የኮሚቴው ሰብሳቢ አብደላ አል ሳድቅ ኮሚቴው ስራውን ያለምንም ችግር እያከናወነ መሆኑን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ላለፉት ሁለት ወራት የደህንነት መስሪያ ቤት (ኢንሳ) መሬቱን የአየር ላይ ፎቶ ሲያነሳ ከርሟል። የአካባቢው ነዋሪዎች ለሚያነሱት ጥያቄ የደህንነት መስሪያ ቤቱ “የመሬቱ ልኬቱ የሚካሄደው ለልማት የሚውለውን መሬት ለመለየት ነው” የሚል መልስ ሲሰጥ ቆይቷል። የደህንነት መስሪያ ቤቱ መሬቱን የማስረከብ ሃላፊነት መውሰዱን ምንጮች ገልጸዋል።