የሱዳን ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና አሜሪካ ከተደረሰው ስምምነት ውጭ እየሄዱ ነው በማለት ድርጊቱን አወገዘ

ኢሳት (ኅዳር 19 ፥ 2009)

የሱዳን ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና አሜሪካ የሱዳን ህዝቦች ነጻነት ንቅንናቄ አማጺ ቡድን መሪ ሪክ ማቻር ከሰላም ስምምነት እንዲወጡ አድርገዋል ሲል ድርጊቱን አወገዘ።

ባለፈው ሳምንት ማቻር ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ወደ መነሻቸው ደቡብ አፍሪካ እንዲመለሱ መደረጉን አስመልክቶ መግለጫን ያወጣው ንቅናቄ ሶስቱ ሃገራት ሪክ ማቻርን ከተደረሰው የሰላም ስምምነት ውጭ ሊያደርጓቸው እንቅስቃሴን እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በአደራዳሪነት በተሳተፉበት የሁለቱ ወገኖች ድርድር የደቡብ ሱዳን መንግስትና በሪክ ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን የጋራ የብሄራዊ የሽግግር መንግስት መመስረታቸው ይታወሳል።

በተደረሰው ስምምነት መሰረትም ማቻር የምክትል ፕሬዚደንት ስልጣን ተሰጥቷቸው ለአንድ አመት ያህል ከቆዩበት አዲስ አበባ ወደ ጁባ እንዲጓዙ ተደርጓል።

ይሁንና ሁለቱ ወገኖች ዳግም ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ሪክ ማቻር ከደቡብ ሱዳን ተሰደው በጎረቤት ሱዳን ቀጥሎም ወደ ደቡብ አፍሪካ በጊዜያዊነት ተጠልለው ይገኛል።

የአማጺ ቡድኑ መሪ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ ወደ ደቡብ ሱዳን የአማጺው ዋና መቀመጫ ፓጋክ የመጓዝ እቅድ እንደነበራቸው ቢነገርም ማቻር የኢትዮጵያ ቪዛ አልያዙም ተብለው ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲመለሱ ተደርጓል።

የሱዳን ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና አሜሪካ ማቻር ከተደረሰው ስምምነት ውጭ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው ሲል ድርጊቱን እንደሚያወግዝ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

አሜሪካ በማቻር እና በሌሎች የአማጺ ቡድኑ አመራር ላይ ማዕቀብ እንዲጣል በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ማግባባትን እያደረገች እንደሆነ ያመለከተው ንቅናቄው ሃገሪቱ ከድርጊቱ ተቆጥባ ለተደረሰው ስምምነት ተግባራዊነት እንድትሰራ ጥሪውን አቅርቧል።

የአፍሪካ ህብረት እና የባራክ ኦባማ አስተዳደር በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ከፈለጉ ሪክ ማቻር በተደረሰው የሰላም ስምምነት ተሳታፊ እንዲሆኑና የተቋረጠው ድርድር እንዲቀጥል ሚናቸው እንዲጫወቱ አክሎ አሳስቧል።