መጋቢት ፳፮ (ሃይ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የሱማሌ ክልል ሦስቱ ርዕሳነ- መስተዳድሮች ከሥልጣናቸው ተሻሩ። የሁለቱ ያለመከሰስ መብት ተነስቷል።
በጅጅጋ ከተማ ከትናትንት በስቲያ በተጀመረው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አራተኛ መደበኛ ጉባዔ ፤ሦስቱም የክልሉ ምክትል ርዕሳነ- መስተዳደሮች ከሥልጣናቸው ተሻሩ፡፡
ቀደም ሲልም ለአንድ ክልል ሦስት ሰዎች ከተሰጣቸው የቢሮ ሃላፊነት ባሻገር በምክትል ፕሬዚዳንትነት ጭምር እንዲሾሙ መደረጋቸው ብዙዎችን ማስገረሙ ይታወሳል።
የክልሉ ምክር ቤት እያካሄደ ባለው አራተኛ መደበኛ ስብሰባ ሦስቱንም ባለስልጣኖች ከምክትል ርዕሰ-መስተዳድርነታቸውም ሆነ ደርበው ከያዙት የቢሮ ሃላፊነት ጠቅላላ ሽሯቸዋል።
ከኃላፊነታቸውና ከሥልጣናቸው የተነሱትም፤ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አህመድ ዴቅ መሐመድ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አደን ፋራህ እና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የእንስሳትና ከፊል እርሻ ምርምር ተቋም ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር ሱልጣን ወሌ መሆናቸውን የአዲስ ዘመን ዘገባ ያመለክታል።
ምክር ቤቱ ባለሥልጣኖቹን ከኃላፊነት ያነሳቸው፤የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸውና በሥራቸው ላይ የአቅም ማነስ ችግር በመታየቱ እንደሆነ ጋዜጣው ጠቁሟል፡፡
በጉባኤው ከሀላፊነታቸው በተነሱት ባለሥልጣናት ምትክ ሌሎች መመረጣቸውን፣ እንዲሁም የምክር ቤቱ አባል የነበሩት የዶክተር አብዲ መሐመድና የአቶ ከበደ በዴ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ መወሰኑንም ዘገባው ጨምሮ ያስረዳል፡፡
በውጥረት ላይ የሚገኘው አቶ መለሰ መንግስት ከወራት በፊት በጋምቤላና በቤንሻንጉሉ ጉሙዝ ክልሎች እንዲካሄድ ባደረገው የምክር ቤቶች ጉባኤ በርካታ ሹም ሽሮችን እንዳደረገና አቶ ያረጋል አይሸሹምን ጨምሮ የሌሎች ሹመኞችን ያለመከሰስ መብት በማንሳት በሙስና ክስ እስር ቤት እንዳስገባቸው መዘገቡ ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide