የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ኅብረት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአፍሪካ ጉብኝታቸው ከዴሞክራሲ መብት ተሟጓቾች ጋር መገናኘት እንዳለባቸው አሳሰቡ

ሐምሌ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ የአፍሪካና የዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾች ኅብረት ማክሰኞ ዕለት ባወጡት የአቋም መግለጫ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በያዝነው ወር በሚያደርጉት የአፍሪካ ጉብኝታቸው ወቅት ከዴሞክራሲ መብት ተሟጓቾች ጋር ፊትለፊት መገናኘት እንዳለባቸው አሳሰቡ።
የሰብዓዊመብት ኅብረት ለሁዋይት ሃውስ በላኩት ደብዳቤ ላይ ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያና በኬንያ ያለውን የመብት ጥሰቶች ሊመለከቱዋቸው ይገባል ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ቡድን፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ሂውማን ራይትስ ወች፣ ፍሪደም ሃውስ፣ኦፕን ሲቲ ፋውንዴሽን፣ሮበርት ኬኔዲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል ባወጡት የጋራ መግለጫ ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው ወቅት ከሰብዓዊ መብት ተከራካሪና ከዴሞክራሲያዊ መብት ተቋማት ጋር መገናኘት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ስድስት ጦማሪያን ታስረዋል፣በኬንያም ሁለት የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ቡድኖች ታግደዋል።በሁለቱም አገራት የሰብዓዊ መብት ምኅዳሩ መጥበቡን ገልጸዋል።
ባራክ ኦባማም ከሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ጋር ለመገናኘት ፍቃደኝነታቸውን አሳይተዋል።
የኬንያው መሪ ኡሁሩ ኬንያታ እንደ ኤውሮፓዊያን አቆጣጠር በ 2007 – 2008 የምርጫ ወቅት በተነሳ ረብሻ ለሞቱ ሰላማዊ ዜጎችና፣ለፈጸሙት ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዓለምአቀፉ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸው የነበረ ቢሆንም በቂ የሆነ መረጃ ያለመገኘቱና የኬንያ ባለስልጣናት ለመተባበር ፍቃደኛ ሆነው ባለመገኘታቸው ክሱ በእንጥልጥል እንዳለ ነው።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የምትፈጽም አገር መሆኗን የአሜሪካ መንግስት በየወሩ በሚያወጣው የመብት ጥሰት ሪፖርት ላይ ከቀዳሚዎቹ ተርታ መገኘትዋና ገዥው ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ የፓርላማ ወንበሮችን በተቆጣጠረበት ወቅት የኦባማ ጉብኝት ማድረግ ግርምታን ፈጥርዋል በማለት አጅንስ ፍራንስ ፕሬስን ጠቅሶ ዘሰንዴይ ዴሊ ዘግቧል።