ኢሳት (ነሃሴ 6 ፥ 2008)
ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በቅርቡ የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና የተመረጠችው ኢትዮጵያ ለድርጅቱ መርሆዎች እንድትገዛ ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል።
ሃገሪቱ ያላት የቆየ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ታሪክ ቋሚ ላልሆነው የተለዋጭ አባልነት አያበቃትም፣ አባል ሆና ከተመረጠችም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቀመጡ አለም አቀፍ ድንጋጌዎችንና ደንቦችን ታክብር ሲሉ ተቋማት በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግስት በጸጥታውና በሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና ብትገኝም ሃገሪቱ እየፈጸመችው ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያ በአባል ሃገራት ዘንድ ጥያቄን ማስነሳት እንዳለበት በሂውማን ራይትስ ዎች ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆንር ይገልጻሉ።
ሃገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል በመሆኗም በሯን ለአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ቡድን ክፍት ማድረግ እንደሚገባት ሃላፊው አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አስመልክቶ በቅርቡ ሪፖርትን ያወጣው ሂውማን ራይትስ ዎች የሃገሪቱ ባለስልጣናት የፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከመደበቅ መቆጠብ ይኖርባቸዋል ሲል አክሎም አሳስቧል።
በተያዘው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኢትዮጵያ ለአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ታዛቢዎች ቡድን ትብብርን እንድታደርግ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፣ መንግስት እምቢታውን መግለጹ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ከቀረበላት ጥያቄ እምቢታዋን ብትገልጽም መቀመጫውን በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ከሃገሪቱ ጋር ድርድር እየተካሄደ እንደሆነ አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በሃገሪቱ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው።