ጳጉሜ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዓለም አቀፍና አገርበቀል የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ድርጅት በኢትዮጵያን እየተፈጸሙ ያሉትን የመብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ በጋራ በደብዳቤ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እየተባበሰ የመጣው ግድያ፣ እስራትና አካል ማጉደል መቀጠሉና የዜጎች ሰላማዊ ሕይወት አስጊ ሁኔታ ላይ መወደቁን ድርጅቶቹ በጋራ አስታውቀዋል። የተመድ የሰብዓዊ መብት ጠቅላላ ጉባኤ በቀጣይ ሴፕቴንበር ከ13 እስከ 30 ቀን 2016 በሚካሄድበት 33ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የመብት ጥሰቶች የመወያያ አጀንዳ እንዲሆኑ ሲሉ ጠይቀዋል።
በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በሁለት ቀናት ብቻ ከመቶ በላይ ንጹሃን ሰላማዊ ሰልፈኞች መገደላቸውን እያየ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ችላሊለው አይገባም ሲሉ በአጽኖት አሳስበዋል። ዜጎች ከጎዳና ላይ ትወስደው ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ አካላዊ ጥቃቶችም ይፈጸምባቸዋል። ይህን የሚያደርጉ የመንግስት የጽጥታ አካላት እና ባለስልጣናት ግን እስካሁን ተጠያቂ አይደሉም ሲሉ በደብዳቤያቸው አትተዋል። እስካሁን በአጠቃላይ ካለፈው ሕዳር ወር ጀምሮ ከአምስት መቶ በላይ ንጹሃን ዜጎች በግፍ መገደላቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ከፍተኛና ቀላል አካዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ድርጅቶቹ አስታውቀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾች፣ ጋዜጠኞች፣ መምህራንን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ ካለህግ አግባብ ለእስራት ተዳርገዋል። እስካሁንም ድረስ ሕገመንግስታዊ መብቶቻቸውን በመጠየቃቸው ብቻ ከታሰሩት ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ የወልቃይት ማንነት ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው አደመን ጨምሮ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ፣ አቶ አለነ ሻማ፣ አቶ አዲሱ ሰርቤ፣ አቶ አታላይ ዛፌ፣ አቶ መብራቱ ጌታሁን፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ አዲሱ ቡላላ፣ የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጠኛ አቶ ጌታቸው ሽፈራው፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የመንግስት ራዲዮ ጋዜጠኛው አቶ ፍቃዱ ሚርቃና አመጹን ተከትሎ ከሕግ ውጪ ከታሰሩት ውስጥ ይጠቀሳሉ።
በኢትዮጵያ ያለው ገዢ መንግስት ሁኔታዎችን ለማርገብ አማራጮችን ከማቅረብ ይልቅ በሃይል ለመፍታት የሚያደርገውን አፈና ገፍቶበታል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች የመብት ጥሰቶቹን በገለልተኛ አካላት እንዲያጣራ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የክተት ጥሪ እንዲቆም ሲሉ ጠይቀዋል።
ጥሪያቸውን ያቀረቡት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና ግብረሰናይ ድርጅቶች አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስወች፣ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ማኅበር፣ ወርልድ አሊያንስ ፎር ሲትዝን፣ ሲቪል ራትስ ዲፌንደር፣ ፍሪደም ሃውስ፣ ዲፌንድ ዲፌንደር፣ ኤፍአይዲኤች (FIDH )፣ ፋውንዴሽን ኦፍ ሂውማን ራይት ኢኒሼቲቭ፣ ኢትዮጵያን ሂውማን ራይት ፕሮጀክት፣ ፍሮንት ላይን ዲፌንደር፣ግሎባል ሴንተር ሪስፖንሲቢሊቲ ቱ ፕሮቴክት፣ ኢንተርናሽናል ሰርቪስ ቱ ሂውማን ራይት፣ ሪፖርተር ዊዝ አውት ቦርደር፣ ዎርልድ ኦርጋናይዜሽን አጌንስት ቶርቸር የመሳሰሉ አስራ አምስት ድርጅቶች ናቸው።