ጥር ፲፭ ( አሥራ አምስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመላ አገሪቱ የሚወጡ አዳዲስ የመከላከያ ሰራዊት የቅጥር ማስታወቂያዎች በወጣቱ ዘንድ ተቀባይነት በማጣታቸው ገዢው ፓርቲ አዳዲስ ስልቶችን እየተጠቀመ ነው። ቀደም ብሎ በየቀበሌዎች የሚጣለው ኮታ ውጤት ባለማምጣቱ አሁን ደግሞ በደላሎች አማካኝት ቅጥር ለመፈጸም ሙከራ እየተደረገ ነው። በመከላከያ ብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ስር የሚታደደረው የቢሸፍቶ አውቶሞቲቭ ሰሞኑን የወታደሮች ቅጥር ማስታወቂያ ቢያወጣም፣ የሚመዘገብ ሰው በመጥፋቱ ፣ ወጣቶች እንዲመዘገቡ ያደረጉ በአንድ ተመዝጋቢ 200 ብር እንደሚከፈላቸው ተነግሯቸው ወጣቶችን የማሳመን ስራ ጀምረዋል።
የተመላሽ ሰራዊት አባላትና ሌሎች የኢህአዴግ አባላት ለዚህ ስራ ተብለው የተመለመሉ ሲሆን፣ አባላቱ ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመሄድ ወጣት ወንዶችና ሴቶች እንዲመዘገቡ የማግባባት ስራ ይሰራሉ። ደላሎቹ ወጣቶችን ለማሳመን ሙከራ ቢያደርጉም፣ ወጣቶች ግን ለመመዝገብ ፈቃደኛ አልሆኑም። ደላሎች ፣ ገንዘቡን ለማግኘት ሲሉ ወጣቶች ከተመዘገቡ በሁዋላ አልፈልግም ማለት እንደሚችሉ እንዲሁም ከሚፈላቸው ላይ ግማሹን እንደሚያካፍሉዋቸው በመግለጽ ለማግባባት እየሞከሩ ነው።
ተቆርቋሪ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ወጣቶች አንድ ጊዜ ከተመዘገቡ በሁዋላ አልፈልግም ማለት እንደማይችሉ፣ ደላሎች “ገንዘብ እንካፈላለን” በማለት የሚያቀርቡትን ማታለያ እንዳይቀበሉ መክረዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላት በየጊዜው እየጠፉ መሆናቸው መከላከያ ከፍተኛ የሰው ሃይል እጥረት ገጥሞታል። አብዛኛው ወታደሮች እረፍት እንኳን ለማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ ቀን ከሌት በተጠንቀቅ ላይ መገኘታቸው፣ እንዲሁም በተቋሙ ውስጥ የሚታየው ዘረኝነት፣ ተቋሙን ጥለው እንዲጠፉ እያስገደዳቸው ነው።
ለአገዛዙ ታማኝ ነው በሚባለው አጋዚ ክፈለጦር ሳይቀር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች በየጊዜው በመጥፋታቸው ክፍለጦሩ እየተመናመነ መሆኑን ከክፍለጦሩ የለቀቁ ወታደሮች ይናገራሉ።