(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 20/2011)ከወር በፊት ያለ ፈቃድ ወደ ቤተመንግስት የተንቀሳቀሱ ወታደሮችን ያስተባበሩ የሰራዊቱ አባላት ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ከወታደራዊ ዲሲፒሊን በማፈንገጥና ሕግን በመጣስ የተንቀሳቀሱትን ወገኖች በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ነገ ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጸም ይከላከላል ሲሉ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ገልጸዋል።
በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር የፍትህ ጉዳዮች ከፍተኛ ሃላፊ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል ኪዱ አለሙ ለመከላከያ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት መረጃ የመሰብሰቡ ስራ ተጠናቆ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
የዛሬ ሳምንት ረቡዕ ህዳር 19/2011 ወታደራዊ ፍርድ ቤት የቀረቡት የሰራዊቱ አባላትን ለፍርድ ለማቅረብ በተደረገው ሒደት ውስጥ በእለቱ ተሳታፊ ከነበሩና ካልነበሩ የሰራዊቱ አባላት ጭምር መረጃ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
እነዚሁ የሰራዊቱ አባላት በምስክርነት ጭምር እንደሚቀርቡባቸውም ከጄኔራሉ መግለጫ መረዳት ተችሏል።
በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ከ284 እስከ 317 በተዘረዘረውና በተለይም ወታደሮችን የተመለከተው የሕግ አንቀጽ በተከሳሾቹ ላይ መቅረቡንም የመከላከያ የፍትህ ጉዳይ ከፍተኛ ሃላፊው ብርጋዴር ጄኔራል ኪዱ አለሙ ገልጸዋል።
በቡራዩ አካባቢ የጸጥታ መደፍረስ ለጥበቃ ተሰማርተው የነበሩት የመከላከያ ሰራዊት አባላት መስከረም 30/2011 ግዳጃቸውን ጨርሰው ወደ ሃዋሳ በሚመለሱበት ወቅት በድንገት ወደ ቤተመንግስት ማቅናታቸው ይታወሳል።
ይህም እንቅስቃሴ ድንገተኛ ያልነበረና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ለመግደል ያለመ መሆኑን የመከላከያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድም አላማው እሳቸውን ለመግደል የተቀነባበረ መሆኑን መግለጻቸውም አይዘነጋም።