የሰሜን ጎንደር የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ የዘር ፍሬያቸውን በመመታታቸው ለህመም እንደተዳረጉ ተናገሩ
(ኢሳት ዜና መጋቢት 27 ቀን 2010 ዓ/ም) አቶ ሙላት ፍሰሃ እንደተናገሩት በጎንደር የተካሄደውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ ተይዘው ከታሰሩ በሁዋላ በማዕከላዊ እስር ቤት ሌሊት ሌሊት እየተጠሩ መደብደባቸውን ተናገሩ።
“ቴዲ ከሚባል ሽፍታ ጋር ተገናኝተሃል፣ ከአርበኞች ግንቦት7 አመራሮች ጋር በመገናኘት በጎንደር ማረሚያ ቤት ላይ ጥቃት ልትፈጽም ነበር” የሚል ውንጀላ የቀረበባቸው ሲሆን፣ ይህንን ውንጀላ አምነው እንዲቀበሉ ለማስገደድ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል። አቶ ሙላት ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ሲናገሩ መርማሪዎች ድብደባ እንደጀመሩ ተናግረዋል። “ ግድግዳ ግፉ” እንደተባሉና፣ ግድግዳ እንዴት ይገፋል ብለው ሲጠይቁ፣ “ ኢህአዴግ እንደ ግድግዳ ነው፣ አይገፋም” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው የተናገሩት አቶ ሙላት፣ ግድግዳውን እንዲይዙ ከተደረጉ በሁዋላ፣ ከሁዋላቸው ተረከዛቸው ላይ በሃይል መመታታቸውንና ወደ ሁዋላ መውደቃቸውን ተናግረዋል።
ወደ ሁዋላ ሲወድቁም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከዚህም እንደገና እንዲነሱና ግድግዳውን ወጥረው እንዲይዙ መደረጋቸውን የሚገልጹት አቶ ሙላት፣ ከጎናቸው ከፍተኛ የሰቆቃ ድምጽ ይሰሙ እንደነበርም ተናግረዋል። ግድግዳውን እንደያዙ የዘር ፍሬያቸውን በማስመሪያ ሲመቱዋቸው ራሳቸውን ስተው መውደቃቸውንና ከዚያ በሁዋላ የሆነውን ሁሉ እንደማያስታውሱ ተናግረዋል። ጭንቅላታቸውና የጎን አጥንታቸውም ጉዳት እንደደረሰበት ገልጸዋል። የዘር ፍሬያቸው በመጎዳቱም ከወጡ በሁዋላ ህክምና ለመከታተል ሞክረው ቢያስን 30 ሺ ብር እንደሚያስፈልጋቸውና ይህንንም ለማሟላት ባለመቻላቸው አሁንም በህመም እየተሰቃዩ መሆኑን ገልጸዋል።
የ4 ልጆች አባት የሆኑት አቶ ሙላት ከእስር ቤት በሁዋላ ህመማቸው እየጸና በመምጣቱ ኢትዮጵያውያን እንዲረዱዋቸው ተማጽነዋል።
አቶ ሙላት ከብሄራቸው ጋር በተያያዘ መሰደባቸውን፣ በሌሎችም እስረኞች ላይ የማኮላሸት እርምጃ እንደተወሰዱባቸው ፍርድ ቤት ላይ መናገራቸውን ገልጸዋል።