ኢሳት (ጥቅምት 3 ፥ 2008)
በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጉዳይ የሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት የቀረበለትን የሽብር ወንጀል ምርመራ መዝጋቱን የተጠርጣሪው ጠበቃ ለኢሳት ገልጹ።
የኮሎኔል ደመቀ ጠበቃ አቶ መከተ ካሳሁን ለኢሳት እንደገለጹት ቀደም ሲል በሰው መግደል ወንጀል የተጠረጠሩት ደምበኛቸው የምርመራ መዝገብ መስከረም 18: 2009 ተዘግቷል።
ይህም የሆነበትም ምክንያት ዕቃቤ ህግ የምርመራ መዝገቡ ባለቀበት 15 ቀናት ውስጥ በህጉ መሰረት ባለመክፈቱ እንደሆነ ገልጸዋል። አሁን ደግሞ በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩበት የምርመራ መዝገብ የሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛው ፍ/ቤት ጉዳዩን የሜመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ፍ/ቤት ነው በማለት መዝገቡን መዝጋቱን ጠበቃው አስረድተዋል።
ጠበቃ መከተ ካሳሁን ማብራሪያ መሰረት እስካሁን በኮሎኔል ደመቀ ላይ በአቃቤ ህግ የተመሰረተ ክስ የለም። እንደጠበቃ መከተ ገለጻ የሽብር ወንጀልን በሚመለከት የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የሚያይ መሆኑ በአዋጅ ተደንግጓል። ይሁንና በአዋጁ መሰረት የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ይህን ጉዳይ በተመለከተ በክልሉ ለጠቅላይ ፍ/ቤት ምድብ ችሎቶች ውክልና ስለሰጠ ጉዳዩ ወደዚያ ሊያመራ እንደሚችል ጠበቃው አስረድተዋል።
በዚህም መሰረት አሁን ባለው ሁኔታ የሽብር የምርመራ መዝገቡ በሰሜን ጎንደር ከፍተኛው ፍ/ቤት በመዘጋቱ የኮሎኔሉ የዋስትና መብት እንዲከበርላቸው መጠየቃቸውንና ፍ/ቤቱም የአቅቤ ህግ አስተያየትን በመስማት ውሳኔ ለመስጠት አርብ መቀጠሩን ጠበቃው አስታውቀዋል።