የሰሜን ኮሪያው መሪ ቻይናን ጎበኙ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 19/2010) የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በቻይና ጉብኝት ማድረጋቸው ተሰማ።

በባቡር ቻይና መግባታቸውንና ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ ጋር መምከራቸውንም ሁለቱ ሃገራት ይፋ አድርገዋል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ የቻይና ጉብኝት ይፋ የሆነው ኪም ጆንግ ኡን ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ በኋላ መሆኑ ታውቋል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ስልጣን ከያዙበት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 2011 ጀምሮ የመጀመሪያ ነው የተባለውን ጉብኝታቸውን በቻይና ቤጂንግ አድርገዋል።

የኪም ጆንግ ኡን የቻይና ጉብኝትን አስገራሚና አነጋጋሪ ያደረገው ደግሞ ጉዟቸው በባቡር መሆኑና ጉብኝታቸውም ይፋ የሆነው ወደ ሃገራቸው በሰላም መመላለሳቸው ከተረጋገጠ በኋላ መሆኑ ነው።

በዚህ ሚስጥራዊ ጉብኝታቸውም ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂፒንግ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል ይላል ቢቢሲ በዘገባው።

የረጅም ግዜ ወዳጅነት አላቸው በተባሉት ቻይናና ሰሜን ኮሪያ መሪዎች  መካከል በተደረገው ወይይትም የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆን ኡን ሀገራቸው ያላትን የኒዩክለር መጠን ለመቀነስ በቅድመ ሁኔታዎች ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል።

ይህ ሚስጥራዊ ጉብኝት ምናልባትም ኪም ጆንግ ኡን ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ለሚኖራቸው ጉብኝት የቻይናን ድጋፍ ለማግኘት ያለመ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት መኖሩን ቢቢሲ በዘጋባው አመልክቷል።

በቀጠዩ ሚያዚያ መጨረሻ ከደቡብ ኮሪያው መሪ ጋር ይገናኛሉ ተብሎ የሚጠበቀው ኪም ጆንግ ኡን በግንቦት ወር መጀመሪያ ደግሞ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተገናኝተው ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከባለቤታቸው ጋር በባቡር ቻይና የገቡት ኪም ጆንግ ኡን  ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ ጋር የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል።