የሰማያዊ ፓርቲ አባል የነበረችው ሜሮን አለማየሁ አርበኞች ግንቦት ሰባት ተቀላቀለች

ኢሳት (ሰኔ 15 ፥ 2008)

የሰማያዊ ፓርቲ የአዲስ አበባ ም/ቤት አባል የነበረችው ወጣት ሜሮን አለማየሁ በረሃ ወርዳ አርበኞች ግንቦት ሰባት መቀላቀሏን አስታወቀች። ማክሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2008 ዓም ለንቅናቄው ልሳን በሰጠችው ቃለ-ምልልስ እንዳስታወቀችው በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እናመጣለን የሚለው ፅኑ እምነቷ በመክሸፉ መሳሪያ ለማንሳት መገደዷን ገልጻለች።

የኢትዮጵያን በአሲስ ታጣቂዎች የደረሰባቸውን ግድያ በማውገዝ በተጠራው ሰልፍ ላይ መንግስት መወገዙን ተከትሎ ወደ እስር ቤት ከተጋዙ ዜጎች ውስጥ እንዳ እንደነበረች ያስታወሰችው ወጣት ሜሮን አለማየሁ፣ በእስር ቤቱ ውስጥ አሰቃቂ ነውረኛ የምርመራ ሂደቶች እንደበሩ ዘርዝራለች። እስረኞቹን ዕርቃን አድርጎ በተቃራኒ ጾታ ፖሊሶች መመርመርና፣ በሌሎች እስረኞች እንዲታዩ ማድረግም የተለመደ መሆኑንም አመልክቷል።

በእስር ቤት ውስጥ የሚፈጸመው ድርጊት እንኳንስ ወደ ትጥቅ ትግል ወደሌላም የሚመራ ነው ስትልም ተደምጣለች።

ሲቪል ለብሰው ምርመራ ከሚያደርጉት በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮማንደር ጋሻው ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ፖሊስ ደግሞ ኮማንደር አበራ የተባሉት በምርመራው ሂደት ተዋናይ እንደነበሩም ሜሮን አለማየሁ ገልጻለች።

ሜሮን መብቷን ጠይቃ፣ ነጻነቷን ፈልጋ በረሃ እንደወረች ሁሉ፣ ሌሎችም ውጤት ጠባቂ ብቻ ሳይሆኑ፣ የራሳቸውን አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉም ጥሪ አቅርባለች።

ከወጣት ሜሮን አለማየሁ በፊት አርበኞች ግንቦት 7ትን ለመቀላቀል ወደ በረሃ ሲያመሩ የተያዙት ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ፍቅረ ማሪያም አስማማውና እየሩሳሌም ተስፋው፣ በአሁኑ ወቅት በወህኔ ቤት ሆነው ጉዳያቸው በመከታተል ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

እነዚህ ሶስት የሰማያዊ ፓርቲ አመራርና አባላት የነበሩት፣ በሰላማዊ ትግሉ ተስፋ ስንቆርጥ አርበኞች ግንቦት 7ትን ለመቀላቀል መወሰናችን ትክክል ነው ወንጀል አልፈጸምንም በማለት በፍርድ ቤት ጭምር መናገራቸው ብዙዎችን ያስገረመ ክስተት ሲሆን፣ የጀግንነት ተግባር ነው ሲሉ ያሞገሷቸውም ብዙዎች መሆናቸውን ከማህበራዊ መድረኮች መረዳት ተችሏል።