የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በእያንዳንዳቸው የ15 ሺህ ብር ዋስ ተጠየቀባቸው

ነኅሴ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከምርጫው ማግስት ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በፖሊስ ተይዘው የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች እያንዳንዳቸው የ15 ሺህ ብር ዋስ ተጠይቆባቸዋል፡፡ አመራሮቹ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ አራት ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ ፖሊስ በሽብርተኝነት ወንጀል እንደጠረጠራቸው ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
ፖሊስ ‹‹ለግንቦት 7 አባላትን እየመለመሉ ይልካሉ፣ኤርትራ ድረስ ሄደው ስልጠና ወስደዋል፡፡›› የሚል ክስ አቅርቦባቸው የነበር ቢሆንም ለክሱ ምንም አይነት ማስረጃ ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡ አመራሮቹ በበኩላቸው የታሰሩት በሰላማዊ ትግል ጠንካራ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ በመሆናቸው፣ በተለይም በምርጫው ወቅት ፓርቲያቸውን በማስተዋወቅና ህዝብን በማደራጀት ጠንካራ ስራ በመስራታቸው ገዥው ፓርቲ የወሰደባቸው በቀል መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ከመታሰራቸው በፊት የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ከፖለቲካው እንዲርቁ ሲያስጠነቅቁዋቸው እንደቆዩም አስታውቀዋል፡፡
ፖሊስ ላቀረበባቸው ክስ አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ዛሬ ነሃሴ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምርጫው ማግስት እየታደኑ ከታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች መካከል 8ቱ ማለትም ልኡል ሰገድ እምባቆም፣ ፋንታሁን ብዙአየሁ፣ መንግስቴ ታዴ፣ አበረ ሙሉ፣ አዳነ አለሙ፣ ሞላ የኑስ፣ ስማቸው ምንይችልና አበባው አያሌው እያንዳንዳቸው የ15 ሺህ ብር ዋስ አቅርበው እንዲፈቱ ወስኗል፡፡
በተጨማሪ በአማራና በደቡብ ክልል በርካታ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ታስረው እንደሚገኙና በተለይም ከተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ታድነው ከተያዙ በኋላ ባህርዳር ከተማ ውስጥ ታስረው የሚገኙት የፓርቲው አመራሮችና አባላት ከፍተኛ ድብደባ እየተፈፀመባቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል ሲል ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡