የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ ብስራት አቢ በእስር ቤት በደረሰባቸው ድብደባ የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሚገኝ ተገለጸ።
(ኢሳት ዜና የካቲት 21 ቀን 2010 ዓ/ም) በአዲስ አበባ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ አደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ የበሩት አቶ ብስራት አቢ በእስር ቤት ውስጥ በደረሰባቸው ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች ምክንያት የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በማእከላዊ እስር ቤት ክፍል ውስጥ በመርማሪዎች በተፈጸመባቸው ከፍተኛ ድብደባ እግራቸው እና ጆሮአቸው መጎዳቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ በተመሳሳይ ክስ ተከሰው አብረው የታሰሩት አራት ሰዎች ክሳቸው ተቋርጦ በነጻ ይፈታሉ ቢባልም እስካሁ ይፈቱ አይፈቱ የታወቀ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
አቶ ብስራት አቢ ለስራ ጉዳይ ወደ ደሴ ከተማ በሄዱበት የካቲት 10 ቀን 2009 ዓ.ም በደኅንነት አባላት ተጠልፈው ማእከላዊ እስር ቤት ከተወሰዱ በሁዋላ ከአራት ወራት በላይ በቤተሰባቸው እንዳይጎበኙ ተደርገው ነበር። ወጣት መኳንንት ካሳሁን፣ ድርሳን ብርሃኑ፣ ብርሃነ መስቀል አበራና ሁለት ሌሎች ወጣቶች በወቅቱ ከሃይቅ ከተማ ተይዘው አብረዋቸው ለአንድ ዓመት መታሰራቸው ይታወቃል።