የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

ታኀሳስ (አንድ) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-ምክር ቤቱ ህዳር 30/ 2007 ዓም ባወጣው መግለጫ “በሀገራችን ህዝባዊ ሥርዓት ለማምጣትና በህግ የበላይነት የሚያምን መንግስት ለመመስረት በምናደርገው ትግል ሁሉ የሚጠበቅብንን መስዋእትነት ለመክፈልና ሀገራዊ ግዴታችንን ለመወጣት ዝግጁ” ነን ብሎአል።

“ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ ዘጠኝ ትብብር የፈጠሩ ፓርቲዎች በህዳር ወር ያወጡት መርሐ ግብር አንድ አካል የሆነውን የ24 ሰዓት የተቃውሞ የአደባባይ ሰልፍ ለመተግበር ሥራ ላይ የነበሩ አመራሮች፣ አባሎቻችና ደጋፊዎቻችን ላይ አምባገነኑ ስርዓት በወሰደው የግፍ እርምጃ ምክንያት ከፍተኛ ድብደባ” እንደደረሰባቸውና  በጨለማ ክፍል ውስጥ እንደተወረወሩ መግለጫው አስታውሷል።

ሽንት ቤትና ጋራዥ ውስጥ አባሎቻችን መታሰራቸው አልበቃ ብሎ በቤተሰብ እንዳይጠየቁ መደረጉ እንዲሁም በድብደባው ምክንያት ራሳቸውን የሳቱና ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎቻች የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳይችሉ መደረጉን የጠቀሰው የምክር ቤቱ መግለጫ፣  አገዛዙ ይህን ሁሉ ግፍ የሚፈጽመው ለሰላማዊ ታጋዮች ባለው ጥልቅ ጥላቻና ጭካኔ በተሞላበት እርምጃው ከትግሉ ያፈገፍጋሉ ከሚል ስሌት ነው ሰል ያክላል።

” ሆኖም” ይላል መግለጫው ” እኛ ወደ ወደ ትግሉ ስንገባ ትግሉ ምን ያህል መስዋዕትነት እንደሚያስከፍል በሚገባ እናውቀዋለንና የህወሓት/ኢህአዴግ  አገዛዝ የወሰደውና ወደፊትም ሊወስደው የሚችለው ከዚህ የባሰም አረመኔነት የተሞላበት እርምጃ ይበልጡን ያጠናክረናል እንጅ ከትግላችን ቅንጣት ያህል ወደኋላ እንድናፈገፍግ አያደርገንም ብሎአል። ህወሓት/ኢህአዴግ  የሰልፉን ተሳታፊዎች ደብድቦና አፍሶ ባሰረበት ወቅት ‹‹ምንም ችግር ሳይፈጥሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል›› እንዳላለ፣  ከስርዓቱ ቁጥጥር ያልወጣው የህግ አካል ‹‹መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት ወድሟል፡፡›› በሚል ሌላ ክስ ማቅረቡ ፣

ፓርቲያችንና ትብብሩ በጀመረው ሰላማዊ ትግል ህወሓት/ኢህአዴግ መደናገጡን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሷል። መግለጫው በመጨረሻም “በሀገራችን ህዝባዊ ሥርዓት ለማምጣትና በህግ የበላይነት የሚያምን መንግስት ለመመስረት በምናደርገው ትግል ሁሉ የሚጠበቅብንን መስዋእትነት ለመክፈልና ሀገራዊ ግዴታችንን ለመወጣት ዝግጁ ” ነን ካለ በሁዋላ፣ “መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀንለትና የምናከብረው ህዝብ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡” በማለት ደምድሟል።

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ -ኢህአፓ ባወጣው እርምጃ በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ  “ነፃነት በልመና የማትገኝ መሆኑን ያረጋገጠ ብቻ ሳይሆን የወያኔ አገዛዝ በሕዝባዊ ትግል ከሥልጣን እስካልተወገደ ድረስ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችልም በግልፅ ያሳየ ነው።” ብሎአል።

ኢህአፓ የታሰሩት የድርጅት አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፡ ጉዳት ለደረሰባቸው ሁሉ አስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት እንዲደርሳቸው ጠይቆ፣  ስልፉ የተደረገበት ዓላማ ግቡን እስኪመታ ድረስ ሳይቋረጥ ትግሉ

መቀጠል ያለበት መሆኑንም አስታውሷል። ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ በእስር  ላይ የሚገኙት የትብብሩ አባላት የተወሰኑት በዋስ እንዲፈቱ መወሰኑ ታውቋል። ሶስተኛ ከታሰሩት ውስጥ ሜሮንንና ምኞትን ነጥለው እንዲወጡ ቢጠየቁም ሌሎች እስረኞች ግን ሁሉም ካልተፈቱ አንወጣም ብለዋል።

ኮተቤና ቤላ ያሉት በመታወቂያ ዋስ እንዲወጡ ሊደረግ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል።