(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 12/2010)
የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን በኢትዮጵያና በተለያዩ የአለም ክፍሎች ለ81ኛ ጊዜ ታስቦ ዋለ።
የኢትዮጵያ ሰማዕታት ቀን በተለይ 6 ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሰማዕታት ሀውልት ዙሪያ በተለያዩ ስነ ስርዓቶች መከበሩም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ሰማዕታት መታሰቢያ በዓል በጣሊያን ወረራ ጊዜ በጄኔራል ግራዝያኒ ትእዛዝ በሶስት ቀናት ብቻ የተጨፈጨፉ 30 ሺህ ዜጎች የሚታሰቡበት ነው።
በ1929 ለጣሊያን ንጉሳዊ ቤተሰብ አንድ ልዑል በመወለዱ በጀኔራል ግራዚያኒ ትዕዛዝ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ደስታቸውን እንዲገልጹ ትዕዛዝ በመተላለፉ በርካታ ህዝብ በግዳጅ እንዲሰበሰብ ተደርጓል።
ኢትዮጵያዊያኑ አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግን እምቢ ለሀገሬ ብለው የያዙትን የዕጅ ቦንብ በስብሰባው ላይ በነበረው የጣሊያን ጄኔራል ግራዚያኒ ላይ ወረወሩ።
በዚህ ጥቃት ጄኔራል ግራዚያኒ እና በርካታ የፋሽስቱ ባለስልጣናት የመቁሰል አደጋ ደረሰባቸው።
ለፋሽስቱ ያደሩ ባንዳዎችና መኳንቶች፣ የፋሽስቱ ባለስልጣናትና ወታደሮችም በአስደንጋጩ የቦምብ ጥቃት ብትንትናቸው ወጣ።
በዚያን ዕለት የጣሊያን ወታደሮች በግቢው ውስጥ የነበሩትን ኢትዮጵያውያን ያለርህራሄ በጅምላ ጨፈጨፉ።
የካቲት 12 1929 በተፈጸመው በዚህ ጭፍጨፋ 30 ሺህ ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ነው የሚታወቀው።
የመታሰቢያ ቀኑ በአዲስ አበባ ታስቦ ሲውል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን አገዛዙ ወጣቶች የሚያነሱትን ጥያቄ አድምጦ ምላሽ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።
ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን አደራ በማስታወስ የሀገርን ሰላምና አንድነት እንዲያስጠብቅም አሳስበዋል።
መታሰቢያ ቀኑ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በጎንደር እና ደብረሊባኖስ ገዳምም በልዩ ስነስርአት ተከብሯል።
የሰማዕታት መታሰቢያ ቀኑን በተለያዩ አለማት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም አክብረውት ውለዋል።
በዚሁም መሰረት በአሜሪካ 7 ስቴቶች ማለትም አትላንታ፣ዳላስ፣ዴንቨር፣ሚያሚ፣ ኒዮርክ፥ፍሎሪዳ ታምፓ እና በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አክብረውታል።
በሌላም በኩል በእስራኤል ኢየሩሳሌም፥በጣሊያን ሮምና ቤሉኖ እንዲሁም በካናዳ ቶሮንቶና ባንኩቨር በተመሳሳይ ሁኔታ መከበሩ ነው የተነገረው።