(ኢሳት ዜና–ሕዳር 18/2010) በዚምባቡዌ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ የልደት ቀን ብሔራዊ የወጣቶች ቀን ሆኖ እንዲከበር ታወጀ።
ባለፈው ሳምንት ስልጣኑን የተረከቡት ኤመርሰን ናንጋግዋ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከዚምባቡዌ መስራች መሪዎች አንዱ በመሆናቸው ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣን እንዲወርዱ በተደረገ ድርድር 10 ሚሊየን ዶላር የጡረታ ጉርሻ እንደተፈቀደላቸው ዘገባዎች ያሳያሉ።
ባለፈው ሳምንት በጦር ሃይሉና በአስታራቂዎች ግፊትና ድርድር የስልጣን መልቀቂያቸውን አስገብተው ወደ ጡረታ የተሰናበቱት ሮበርት ሙጋቤ 10 ሚሊየን ዶላር የጡረታ ጉርሻ ተቀብለዋል የሚሉ ሪፖርቶች በመውጣት ላይ ናቸው።
የተቃዋሚው ፓርቲ የዲሞክራሲ ለውጥ ንቅናቄ ድርጊቱ ሙጋቤ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ለማግባባት የተሰጠ ጉቦ ነው ሲል ይከሳል።
ዚምባቡዌን ለ37 አመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት ሮበርት ሙጋቤና ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ከ10 ሚሊየን ዶላር የጡረታ ጉርሻ በተጨማሪ ያለመከሰስ መብታቸው ተጠብቆ የተንደላቀቀ ኑሯቸውን እንደሚቀጥሉ ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል የሚለውን ጉዳይ ተቃዋሚው የዲሞክራሲ ለውጥ ንቅናቄ ፓርቲ በፍርድ ቤት እንዲታይ አደርጋለሁ ብሏል።
የሀገሪቱ ሕገ መንግስት በጡረታ የሚገለሉ ፐሬዝዳንቶችን መብት በግልጽ ያስቀመጠ በመሆኑ ተሰጠ የተባለው ጉርሻና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንደ ትልቅ ጉቦ የሚታዩ ናቸው ይላሉ የተቃዋሚው ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ደግለስ ምዎንዞራ።
አክለውም ሲናገሩ ሙጋቤ ከዙፋኑ ለመውረድ ዚምባቡዌያንን ተጨማሪ ወጪ ማስወጣት የለብንም ሲሉ ለስካይ ኒውስ ተነግረዋል።
በዋነኛነት ድርድሩን ያካሄዱት የሮማ ካቶሊኩ ቄስ ፊደሊስ ሙኮሮኒ በድርድሩ ወቅት የተደረሱት ዝርዝር ስምምነቶች ሚስጥራዊ ቢሆኑም የገንዘብ ጉዳይ ግን ዋናው እንደነበር አልሸሸጉም።
ዚምባቡዌያውያን በፕሬዝዳንቱና ቤተሰባቸው የተቀናጣ ኑሮ እጅግ እንደሚበሳጩ ዘገባዎች ያሳያሉ።
የሙጋቤ ባለቤት የግሬስ ወንድ ልጅ በአንድ የምሽት ክለብ ውስጥ የ60ሺ ዶላር ሰአቱ ላይ ሻምፓኝ ሲያፈስ የሚያሳየው ቪዲዮ እንዲሁም የግሬስ ሙጋቤ ስልጣኑን ለመረከብ ያደረጉት ሙከራ የሰራዊቱን አዛዦችና የፓርቲው ዛኑ ፒ ኤፍ አባላትን ያበሳጨ ጉዳይ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዚምባቡዌ መንግስት የፈረንጆቹ የካቲት 21ን የሮበርት ሙጋቤ ብሔራዊ የወጣቶች ቀን ሲል አውጇል።
ቀኑ የሙጋቤ የልደት ቀን እንደሆነ ይታወቃል።
የሙጋቤን የልደት ቀን ብሄራዊ ቀን ለማድረግ በዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ውስጥ ባለው የወጣቶች ሊግ ጉትጎታ አማካኝነት ባለፈው ነሀሴ በመንግስት ተቀባይነት ካገኘ በኋላ በአዲሱ የኤመርሰን ናንጋግዋ መንግስት ዛሬ በይፋ ታውጇል።
ባለፈው ሳምንት ስልጣኑን የተረከቡት ኤምርሰን ናንጋግዋ በዚህ ሳምንት ካቢኔያቸውን ያዋቅራሉ ተብሎ ይጠበቃል።