“የራያ ህዝብ የአማራ ማንነት ይከበር” ሲሉ የአላማጣና አካባቢው ተወላጆች ጠየቀ

“የራያ ህዝብ የአማራ ማንነት ይከበር” ሲሉ የአላማጣና አካባቢው ተወላጆች ጠየቀ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 27 ቀን 2010 ዓ/ም) ሰሞኑን በራያ ወረዳ አላማጣ ከተማ በመገኘት የአካባቢውን ህዝብ ያነጋገሩት የራያ ተወላጁ የህወሃት ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ፣ ከተስብሳቢዎች ጠንካራ ጥያቄዎች እና ተቃውሞ ያጋጠማቸው መሆኑን ተከትሎ፣ ስብሰባውን ያለውጤት በትነው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።
ከ400 በላይ ወጣቶች በተገኙበት በዚህ ስብሰባ ላይ ወጣቶች አቶ ጌታቸውን ረዳን “በአማርኛ አናግረን፣ በትግርኛ የምታናግረን ከሆነ ግን አንቀበልም” ያሉት ሲሆን፣ “አንተ አገርህን የሽጠህ ህዝብን የካድህ” ነህ ሲሉ ነቅፈውታል። አቶ ጌታቸው በትግርኛ ሲናገር፣ ሁሉም ተሰብሳቢዎች በአማርኛ የተናገሩ ሲሆን፣ የራያ ተወላጆች በህወሃት ትዕዛዝ በቦንብ ጭስ ሲታፈኑ ከመኖሪያ ቀያቸው ሲፈናቀሉና ከፍተኛ በደሎች ሲደርስባቸው የአንተም እጅ አለበት በማለት ወቅሰውታል።
“ከፊትም ራያ ወሎ እንጅ ትግራይ ሆኖ አያውቅም፣ ባህሉም ቋንቋውም የታወቀ ነው፣ በራያነቱ ነው እንጅ በትግራይነቱ አያምንም፣ አሁንም በመሳሪያ ተገደን በትግራይ ክልል እየተመራ ነው” ብለዋል።
የራያ ህዝብ ጥያቄ ምንድነው ተብለው የተጠየቁት ሌላው የአካባቢው ተወላጅ በበኩላቸው፣ የአካባቢው ህዝብ ጥያቄ፣ “ እኛ ትግሬ አይደለንም፣ ድሮም ራያ ቆቦ ነው የነበርነው፣ ራያ ልዩ ዞን ትሁንልን” የሚል ነው ብለዋል።