(ኢሳት ዜና–ጳጉሜ 1/2009) በባህርዳር ከተማ የራህ ናይል ሆቴል በባለቤትነት ከባለስልጣናት ጋር የተያያዘ ነው በሚል የተላለፈው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ቅርበት ያላቸው ምንጮች በሰነድ አስደግፈው በላኩልን መረጃ አመለከቱ።
በባህር ዳር ቀበሌ 05 ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የሚገኘው ራህናይል ሆቴል የተገነባው ለ20 አመታት በምህንድስናና የማማከር አገልግሎት እንዲሁም በዲዛይን ስራና በግንባታ ዘርፍ ሙያ በተሰማሩና አቶ አበበ ይመኑ በተባሉ አርክቴክት አማካኝነት እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።
በ4 መቶ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ባለ አራት ፎቅ ሕንጻ ሆቴል በባህርዳር ከተማ የተገነባው ከሁለት የግል ባንኮች ጋር በተደረገ የብድር ስምምነት መሆኑን የደረሰን ሰነድ ያመለክታል።
ባለሃብቱ ብድሩን መክፈል አቅቷቸው ከ3 ባንኮች ጋር በተደረገ የብድር ልውውጥ እየተዘዋወረ የመጣና በመጨረሻም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕዳ ያለበት መሆኑን መገንዘብ ተችሏል።
ራህናይል ሆቴል በግለሰቡ ጥረት የተገነባ ሆኖ እያለ አባለሃብቱ ቤተሰብ ከባለስልጣናት ጋር ያላቸውን ግንኙነት መነሻ በማድረግ የተሰራ ነው መባሉን በዚሁ ሰነድ አስተባብለዋል።
በባህር ዳር ከተማ የተገነቡ የተወሰኑ በስም የተጠቀሱ ዘመናዊ ሆቴሎች ከአገዛዙ ባለስልጣናት ጋር ቅርበት ባላቸው ሰዎች ስም በእጅ አዙር የተገነቡ መሆናቸውን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።