የሪፐብሊካን እጩ ተወዳዳሪ ዶናልድ ትራምፕ ማሽነፋቸውን ተከትሎ የአለም ኢኮኖሚ እየዋዠቀ ነው ተባለ

ኢሳት (ጥቅምት 30 ፥ 2009)

የአሜሪካው የሪፐብሊካን እጩ ተወዳዳሪ ዶናልድ ትራምፕ ቀጣዩ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ለመሆኝ መብቃታቸውን ተከትሎ በአውሮፓና በተለያዩ የአለማችን አህጉራት ኢኮኖሚያዊ መዋዠቅ መከሰቱ ተነገረ።

ባልተጠበቀ ሁኔታ ለድል በቅተዋል የተባሉት እና የፖለቲካ ዕውቀት የላቸውም የሚል ስሞታ ሲቀርብባቸው የነበሩት ተመራጩ ፕሬዚደንት ተግባራዊ አደርገዋለሁ ሲሉ የነበሩት የኢኮኖሚና ኢሚግሬሽን ፖሊስ ለአለም ሃገራትና ለአሜሪካ አዲስ ምልከታ መፍጠሩን ሮይተርስ ዘግቧል።

በአለም ዙሪያ ግዙፍ የሚባሉ የንግድ ተቋማት እና ባለሃብቶች አዲሱ ፕሬዚደንት ተግባራዊ ሊያደርጉት የፈለጉት አዲስ የኢኮኖሚ አካሄድ ኢንቨስትመንታቸው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

በኤዢያና በአውሮፓ የአለም የአክሲዮን ግብይት መዋዠቅን ያሳየ ሲሆን፣ የተለያዩ ባለሃብቶች ገንዘባቸውን በወርቅና በሌሎች አማራጮች ለመለወጥ መወሰናቸውን የፋይናንስ ተቋማት ገልጸዋል።

45ኛ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የበቁት ዶናልድ ትራምፕ በተለይ ሃገራቸው ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስናት የድንበር ግዛት አጥር ለማጠር የያዙትን እቅድ በሜክሲኮ አዲስ ስጋት ማሳደሩም የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል።

የሜክሲኮ የመገበያያ ገንዘብ የሆነው ፔሶ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅም በስድስት በመቶ አካባቢ ቅናሽ ማሳየቱንም BBC ረቡዕ ዘግቧል።

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ረቡዕ ረፋድ ድረስ በታወቀ አጠቃላይ ድምፅ ለማሸነፍ ከሚፈለገው 270 ውጤት ውስጥ 289 ማግኘት የቻሉ ሲሆን፣ የዴሞክራት እጩ ፕሬዚደንታዊ ተወዳዳሪ የነበሩት ሂላሪ ክሊንተን 218 (ኤሌክቶራል ቮትስ) የምርጫ ድምጽ አግኝተዋል።

ረቡዕ ንጋት ላይ ለድል መብቃታቸውን ያወጁት ተመራጩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከምክትላቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ለአሜሪካዊያን የድል ንግግር አቅርበዋል።

ባለሃብቱ ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው ሁሉንም የአሜሪካ ዜጋ በእኩልነት እንደሚመለከቱና ለአንድነት መስፈን ጥረትን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

ለድል ያልበቁት ሂላሪ ክሊንተን ከድሉ በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ንግግርን ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሲጠበቅ የነበረውን ንግግር ሳያቀርቡ ለተመራጩ ፕሬዚደነት ስልክ በመደወል ዕውቅናን እንደሰጡ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ለሂላሪ ክሊንተን ቅስቀሳን ሲያደርጉ የሰነበቱት ተሰናባቹ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ለሚተኳቸው አዲሱ ፕሬዚደንት ድል መብቃት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕከትን አቅርበዋል።

የ70 አመቱ ትራምፕ ሃሙስ ከፕሬዚደንት ኦባማ ጋር ለመምከር ቀጠሮ የተያዘላቸው ሲሆን፣ የተለያዩ ሃገራት ለፕሬዚደንቱ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት በማስተላለፍ ላይ መሆናቸውም ታውቋል።