(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 27/2010)
የሩሲያ የመንገደኞች አውሮፕላን ዛሬ በሶሪያ ውስጥ መከስከሱ ተሰማ።
በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 26 መንገደኞችና 6ቱ የአውሮፕላን ሰራተኞች በሙሉ ማለቃቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።
በሶሪያ የባህር ዳርቻ በምትገኘው ላታኪያ ከተማ ባለው የሩሲያ ወታደራዊ ጦር ሰፈር በማረፍ ላይ እያለ አውሮፕላኑ መከስከሱም ታውቋል።
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ሲሆን የቅድመ ምርመራ መረጃዎች አደጋው በቴክኒካል ችግር ሳይከሰስ እንዳልቀረ አመላክተዋል።
ሆኖም እውነተኛውን የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ ምርመራው ቀጥሏል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
በምርመራው ሒደት አውሮፕላኑ ምንም አይነት ጥቃት እንዳልተፈጸመበት ተረጋግጧል።
አንቶኖቭ 26 በተባለው በዚህ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩትን የአውሮፕላኑን ሰራተኞች ጨምሮ 32 ሰዎች በአደጋው ማለቃቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አረጋግጧል።
ሩሲያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ የበሽር አላሳድን መንግስት በመደገፍ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኗ ይታወቃል።
ከአመት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በታህሳስ 2016 የሩሲያ ወታደራዊ ኦርኬስትራን ባንድ ጭኖ ወደ ሶሪያ ሲጓዝ የነበረ አውሮፕላን ጥቁር ባሕር ላይ ተከስክሶ 92 ተሳፋሪዎች ማለቃቸው ይታወሳል።