የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላን በጥቁር ባህር ላይ ተከሰከሰ

ኢሳት (ታህሳስ 17 ፥ 2009)

ንብረትነቱ የሩሲያ የሆነ ወታደራዊ አውሮፕላን ዕሁድ በጥቁር ባህር ላይ ተከሰከሰ። የገቡበት ያልታወቀ ከ90 በላይ ሰዎችን ለማግኘት ዘመቻ በመካሄድ ላይ መሆኑን ሩሲያ አስታወቀች።

ይኸው ወደ ሶሪያ በማቅናት ላይ የነበረው አውሮፕላን ወታደሮችን፣ ሙዚቀኞችን፣ እንዲሁም ጋዜጠኞችና የበረራ ባለሙያዎችን ይዞ በማቅናት ላይ እንዳለ ሶቺ ተብላ ከምትጠራ የባህር ዳር አቅራቢያ ከተማ መከስከሱን የሩሲያ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

የሃገሪቱ ወታደራዊ ባለስልጣናት ወታደራዊ አውሮፕላኑ 92 የሚሆኑ ሰዎችን አሳፍሮ እንደነበር ያስታወቁ ሲሆን፣ የመከስከስ አደጋው በምን ምክንያት የደረሰ እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ከ100 የሚበልጡ ጥልቅ ዋናተኞችን ጨምሮ መርከቦች፣ አውሮፕላኖችና፣ ሄሊኮፕተሮች በነፍስ አድን እና አውሮፕላኑ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን፣ በእስካሁን ፍለጋ የ11 ሰዎች አስከሬን መገኘቱ ታውቋል።

መንገደኞቹን በነፍስ የማግኘቱ ዕድል ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ የሚናገሩት የነፍስ አድን ሰራተኞች ከአስራ አንዱ አስከሬን በተጨማሪ 154 የሚደርሱ የሰውነት ክፍሎች መገናኘታቸውንም ይፋ አድርገዋል።

የሩሲያ የመከላከከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ሜጀር ጄኔራል ኢጎር ካናሼንኮቭ የፍለጋው ዘመቻ ለ24 ሰዓት ያለማቋረጥ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በፍለጋው የተገኙ 10 አስከሬኖች እና 86 የሰውነት ክፍሎች ወደ ሞስኮ በመጓጓዝ ማንነታቸውን የመለየት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ቃል-አቀባዩ አክለው አስታውቀዋል።

ቱፓልብ-154 የሚል መጠሪያ ያለው ይኸው ወታደራዊ አውሮፕላን ከሶቺ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ከተነሳ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ከአየር ትራፊክ ጋር የነበረው ግንኙነት የተቋረጠ ሲሆን፣ አደጋው የሽብር ድርጊት እንደማይሆን ይታመናል ሲሉ የሩሲያ የትራንስፖርት ባለስልጣናት ለመገኛኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

ባለስልጣኑ አደጋው ከሽብር ጋር እንደማይያያዝ ቢገልፁም ለአውሮፕላኑ መከስከስ የሰጡት ምክንያት አለመኖሩን ዘግቧል።

መነሻውን ከሞስኮ አድርጎ የነበረው ወታደራዊ አውሮፕላኑ በሶቺ ከተማ ነዳጅ ለመሙላት አርፎ እንደነበር የሚናገሩት ባለስልጣን መንገደኞቹ በሶሪያ ለሚገኙ የሩሲያ ወታደሮች የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ በማቅናት ላይ እንደነበሩ ገልጸዋል።

የአደጋው መድረስ ተከትሎ ሩሲያ ሰኞ የሃዘን ቀን እንዲሆን የደነገገች ሲሆን አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን ላለፉት 33 አመታት ጥገናዎች እየተደረጉለት በአገልግሎት ላይ እንደነበር ታውቋል።

ሩሲያ አውሮፕላኑ ለሲቪል አገልግሎት የማትጠቀመው መሆኑም ተነግሯል። ይሁንና ቱፓልቭ-154 የተሰኙ 50 አውሮፕላኖች በአሁኑ ወቅት በሩሲያና በጥቂት ሃገራት ውስጥ አገልግሎት ላይ እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል።