(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 9 /2010) 1 ሺህ 439ኛው የረመዳን ጾም ዛሬ በመላው ዓለም ተጀመረ።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የረመዳንን ጾም ሰደቃ በማብዛት፣ የታመሙትን በመጠየቅና ከተቸገረው ጎን በመሆን ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ የሃይማኖት አባቶች ጠይቀዋል።
የጾም ወቅቱ ከሚፈቅዳቸው በጎ ምግባራት ጎን ለጎን ሙስሊሙ ማህበረሰብ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሃይማኖት አባቶች ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብይ አህመድ ደግሞ ዛሬ የጀመረውን የረመዳን ፆም በማስመልከት ለመላ የእስልምና እምነት ተከታዮች ‘የእንኳን አደረሳችሁ’ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የረመዳን ፆም ለኢትዮጵያ ሰላም እና እድገት፣አንድነትና ብልጽግና በትጋት የሚጸለይበት ወር እንዲሆን ተመኝተዋል።
“ጾሙ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከፈጣሪ ጋር ግንኙነት የሚያደርግበት በመሆኑ ለአገርና ህዝብ የሚበጅ ሀሳብና በተጨባጭ ወደ መሬት የሚወርድ ተግባር ለማከናወን እድል ይሰጣል” ብለዋል።
1 ሺህ 439ኛውን የረመዳን ጾም በተለያዩ የህይወት አጋጣሚዎች የተቀያየሙ ሰዎች ይቅር እንዲባበሉ በማግባባትና አብሮነትን የሚያጠናክሩ የኃይማኖቱን እሴቶች አክብረው እንደሚያሳልፉ የኃይማኖቱ ተከታዮች ገልጸዋል።
በከተማዋ ከሚኖሩ የኃይማኖቱ ተከታዮች መካከል ሼህ አህመድ ሼህ ሀሰን እንዳሉት ጾሙን የሚያሳልፉት ለሰው ልጆች ሁሉ ደግ ደጉን በመስራት ነው፡፡
“ በታላቁ የረመዳን ወር ከቤተሰቦቻችን ጀምረን ለሁሉም የሰው ልጅ መልካም ስራ የመስራት ተግባራችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን “ብለዋል ።
የእስልምና ኃይማኖት ለሰላም የሚሰጠው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ለአካባቢያቸው ሰላም መጠበቅ ህዝበ ሙስሊሙ በተለየ መልኩ በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል።
አቶ አባቢያ አባሞጋ የተባሉ ሙስሊም በበኩላቸው የታላቁን የረመዳን ወር ከቤተሰቦቻቸውና ከጎሮቤቶቻቸው ጋር በደስታ፣ መልካም ተግባር በማከናውንና ኃይማኖታዊ ስርዓቱን በመፈጸም ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመላው አለም ለሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች መልካም የጾም ጊዜ ይሁንላችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።