የሥነ-ምግባር መኮንኖች ተወቀሱ

ሐምሌ ፲(አስር)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጽያ የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ትግሉን እንዲያግዙና የሥነ ምግባር ትምህርቶችን በየተቋሞቻቸው እንዲያሰርጹ በመንግስት መ/ቤቶች የተቋቋሙ የስነምግባር መከታተያ ክፍሎች በባለሙያዎች የተሠጣቸውን ተልዕኮ እየተወጡ አለመሆኑ ተሰምቷል፡፡
የሥነ-ምግባር መኮንን ተብለው በየመንግስት መ/ቤቶች የተቀመጡት እነዚሁ ባለሙያዎች በየተቋማቸው ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመዋጋት እንዳልቻሉ ሰሞኑን ባካሄዱት ስብሰባ ላይ በይፋ አምነው ተቀብለዋል፡፡ የፌዴራል የሥነምግባርና ጸረ ሙስና ኮምሽን በጠራው በዚሁ ስብሰባ ላይ መኮንኖቹ ኃላፊነታቸውን ካለመወጣታቸውም በላይ አንዳንዶቹ
ለስነምግባርና ለሙስና ችግሮች ተጋልጠዋል መባሉም ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

የሥነምግባር መኮንንኖቹ ተጠሪነት ለመ/ቤት የበላይ ኃላፊዎች መሆን᎐ ሥራቸውን በነጻነት ለመስራትና የበላይ ኃላፊዎችን ሙስናና ብልሹ አሰራር ተከታትሎ ለማጋለጥ አመቺ አለመሆኑን አንድ መኮንን ለዘጋቢያችን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በብዙዎቹ መ/ቤቶች የስነምግባር ክፍሎች   ከመከፈታቸው ውጪ በተገቢው መንገድ ስራቸውን ባለማከናወናቸው የብዙሃኑን ሰራተኛ አመኔታ እንኳን ማግኘት አለመቻላቸው ታውቋል፡፡

መኮንኖቹ በኮምሽኑ በኩል የሚደረግላቸው ድጋፍና ክትትል አነስተኛ መሆንም  ስራቸውን በተገቢው መንገድ ላለመወጣታቸው አንድ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ኮምሽኑ የስነምግባር መኮንኖቹ አቅም ፈጥረው በየቋሞቻቸው ሙስናና ብልሹ አሰራርን እንዲዋጉ፣ የስነምግባር ትምህርቶችን እንዲያስፋፉ፣ የተጣለባቸውንም ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስቦአቸዋል፡፡