የሞዛንቢክ ፖሊስ ሕገወጥ ናቸው ያላቸውን 23 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን መያዙን አስታወቀ
(ኢሳት ዜና የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ/ም)ከሞዛንቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ማኒካ አውራጃ አቆራርጠው በሕገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊገቡ የሞከሩ 23 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአገሪቱ ፖሊስ ገልጿል።
የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አቶ ጆርጌ ማቻቫ ”ኢትዮጵያዊያኑን ስደተኞች በተኙበት ይዘናቸዋል። በአሁኑ ወቅትም በቫንዱዚ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በእስር ላይ ይገኛሉ። ስደተኞቹ በረዥምሙና ድካሚው ጉዞ ምክንያት አካላቸው ተጎሳቁሎ የታረዙና የገረጡ ናቸው። የሥራ እድል ማጣትና የድኅነት ኑሮ ሕይወት ነው ይህን ዓይነት አስቸጋሪ ጉዞ ያስመረጣቸው።” ብለዋል።
ሞዛንቢክ ያለችበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ባላት የተፈጥሮ ሃብት ምክንያት የአገሪቱ ድንበር ለህገወጥ ስደተኞች የተጋለጠ ነው። ፖሊስ ይህን ተገንዝቦ ችግሩን ለመቅረፍ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑንም አቶ ጆርጌ አክለው አስረድተዋል።
በቅርብ ወራት ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሞዛንቢክ የገቡ አራት ሽህ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ስደተኞች ከሞዛቢክ ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውን ቪኦ ኤን ጠቅሶ ዘ ኢስት አፍሪካንስ ዘግቧል።
በገዥው ህወሃት/ኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ባሉት የብዙሃን መገናኛዎች ለወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩንና አገሪቱ ባለሁለት አሃዝ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እንዳመጣች በተደጋጋሚ ይነገራል። ነገርግን ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በአገራቸውን በሚደርስባቸው አፈናና መገለል ተስፋ እየቆረጡ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው መፍለሳቸውን አላቋረጡም።