የምግብ ሸቀጣ-ሸቀጦች ዋጋ 6.3 በመቶ ማደጉ ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 25 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ የምግብ ነክ በሆኑ ሸቀጣሸቀጦች ላይ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ተከትሎ የሃገሪቱ ምግብ ነክ የሆኑ ሸቀጣሸቀጦች ዋጋ በ 6.3 በመቶ ማደጉ ተገለጠ።

በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ የምግብ እጥረት እንዲከሰትና የዋጋ ጭማሪን በማስከተሉ ምክንያት የባለፈው ወር የዋጋ ግሽበት ከአንድ በመቶ በላይ ማደጉ ታውቋል።

በተመሳሳይ ህኔታም ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጣሸቀጦች ላይ የ8.7 በመቶ የዋጋ ጭማሪ የተመዘገበ ሲሆን እድገትን እያሳየ የመጣው አጠቃላይ የሸቀጣሸቀጦች ዋጋ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እንደሚያሳድር የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በሃገሪቱ በስድስት ክልሎች የተከሰተው የድርቅ አደጋና የውጭ ንግድ ገቢ ማሽቆልቆል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እየተፈታተነው እንደሚገኝም እነዚሁ ባለሙያዎች አስረድተዋል።

በሁለት አህዝ እድገት ያመጣል ተብሎ በመንግስት የተተነበየው የኢኮኖሚ እድገትም በዚሁ ችግር ምክንያት ወደ አምስት በመቶ ሲያሽቆለቁል እንደሚችሉ የተለያዩ የገንዘብ ተቋማት በቅርቡ ይፋ አድርገዋል።

የአለም ባንክ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠርና የውጭ ምንዛሪ እጥረ ችግርን ለመቅረፍ የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን መውሰድ እንዳለባት ሲያሳስብ መቆየቱም ይታወሳል።

የሃገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበትም 7.4 በመቶ መሆኑ ታውቋል።