ኢሳት (ጥር 17 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከሃገር ውስጥ እና ከውጭ አበዳሪ አካላት የወሰደው ብድር ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱንና ብድሩ የበጀት እጥረት ውስጥ እንደከተተው ይፋ አደረገ።
ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወር ስራ አፈጸጸሙን አስመልክቶ ሪፖርቱን ያቀረበው ኮርፖሬሽኑ በተያዘው በጀት አመት የተለያዩ ስራዎችን ለማከናወን ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ለማግኘት ፍላጎት ቢኖርም 31 በመቶ ብቻ የሚሆነው ገንዘብ ከሃገር ውስጥ ሊገኝ እንደሚችል ፍንጭ መገኘቱን ሪፖርተር ዘግቧል።
ይሁንና የኢትዮጵያ ምድር ኮርፖሬሽን ወደ 26 ቢሊዮን ብር (አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ) ከውጭ አገር የፋይናንስ ተቋማት ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ገንዘቡን ሊያገኝ እንዳልቻለና በከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት ውስጥ መሆኑን ለፓርላማ ገልጿል።
ከጥቂት አመታት በፊት በአዲስ መልክ የተቋቋመው ይኸው መንግስታዊ ተቋም የኮርፖሬሽኑ የእዳ ክምችት ባለፈው አመት ከነበረበት 96 ቢሊዮን ብር አካባቢ ወደ 103 ቢሊዮን ብር ማደጉን በቀረበው ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎችና እስከ ጅቡቲ ድረስ የሚደርስ የባቡር መስመር በቅርቡ የገነባው ኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የሆነ የወለድና የግዴታ ክፍያ በየአመቱ ለውጭ ባንኮች እየከፈለ እንደሚገኝ ለፓርልማ ማስረዳቱን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለአዲስ አባባ ጅቡቲ የባቡር ፕሮጄክት ለተበደረው 2.5 ቢሊዮን ዶላር የወለድና ግዴታ ክፍያ መክፈል ቢጀምርም በቅርቡ የተመረቀው ፕሮጄክት ወደ ስራ አለመግባቱ ተመልክቷል። ይሁንና የባቡር መስመር በሶስት ወራት ውስጥ ስራውን ይጀምራል ተብሏል።
ከወራት በፊት 35.4 ሚሊዮን ዶላር እዳ መከፈሉን ያወሳው ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በበጀት እጥረትና የእዳ ጫና ፈተና ውስጥ እንደከተተውም አስረድቷል።
ኮርፖሬሽኑ በተያዘው ወር 45 ሚሊዮን ዶላር እዳ መክፈል የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ይህንን ግዴታውን ለመወጣት የውጭ ምንዛሪውም ሆነ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮች በግልጽ አለመታወቁን ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት አስፍሯል። በቅርቡ ስራውን በከፊል የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር አገልግሎት እስካሁን ድረስ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት ተመልክቷል።
የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ፕሮጄክትን ጨምሮ ኮርፖሬሽኑ በተያዘው ወር መክፈል የሚገባው የብድርና ወለድ ክፍያ 96 ሚሊዮን ዶላር (2.2 ቢሊዮን ብር) አካባቢ መሆኑንም ታውቋል።
ይሁንና መንግስታዊ ድርጅቱ ይህንን እዳ ከየት አምጥቶ እንደሚከፈል አጣብቂኝ ውስጥ ሲሆን፣ ድርጊቱ በኮርፖሬሽኑ ላይ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌታቸው በትሩ (ዶ/ር) ለፓርላማ አስረድቷል።
የአለም ባንክ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የውጭ ንግድ ገቢ ማሽቆልቆልን ለመታደግ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን መውሰድ እንዳለባት በማሳሰብ ላይ ሲሆን፣ የሃገሪቱ አጠቃላይ የብድር እዳ ክምችት ከ36 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱም በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል።
መንግስት ባጋጠመው የፋይናንስ ቀውስና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ተጨማሪ ብድር የመጠየቅና የመውሰድ አቅሙ ስጋት ውስጥ መግባቱን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የባህረ ሰላጤ ወዳጅ ሃገራት ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ እንዲያስቀምጡ በመደረግ ላይ መሆኑን መግለፅ ይታወሳል።
ይሁንና መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠበ ሲሆን፣ ያጋጠመው የፋይናንስ እጥረት በሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶች ላይም ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በቅርቡ ይፋ አድርጓል።