የምእራብ አርሲ ወጣቶችን ለመያዝ የተሰማራው የአጋዚ ጦር ቤት ለቤት በመግባት አሰሳ እያደረገ ነው

ሐምሌ  ፲፱ ( አሥራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በከኮሳ፣ አሰሳና ዶዶላ አካባቢዎች ሃምሌ 18 እንደገና የተጀመረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የመንግስት መስሪያ ቤት የወደመ ሲሆን፣ መንገዶችም ተዘግተው የተሽከርካሪ እንቅስቃሴም ተቋርጦ ውሎአል። የፌደራል ፖሊስ አባላት መኪኖች ወደ ከተሞች መግባት ባለመቻላቸው በእግራቸው ተጉዘው ለመግባት የቻሉ ሲሆን፣ ምሽት ላይ ጥይቶችን በመተኮስ ህዝቡን ሲያሸብሩት አምሽተዋል።

ዛሬ ደግሞ ቤት ለቤት እየገቡ ወጣቶችን በማሰር ላይ ሲሆን፣ በርካታ ወጣቶች ጫካ መግባታቸው ታውቋል። እነዚህም ወጣቶች የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱ እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል:: በቦረና ዞን በሚዮ እና ድሬ ወረዳዎች ተቃውሞ ሲካሄድ መዋሉንና ህዝቡ ከእንግዲህ በህወሃት አንገዛም በማለት ተቃውሞ ሲያሰማ መዋሉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በምስራቅ ሀረርጌ በጋረሙለታ ጉራዋ ወረዳ ዶጉ ወይም አንቦጢቆ በምትባል ከተማ ትናንት ምሽት ላይ ሕዝባዊ ተቃውሞው ተካሂዷል።