ህዳር 29 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቅርቡ በአማራ ክልል “የህዝብን ቅሬታ ለማስታገስ” በሚል ምክንያት ፣ ብአዴን በክልሉ ያካሄደው ግምገማ ንቅናቄው ያልጠበቃቸው ነገሮች በመከሰታቸው ግምገማውን ለመሰረዝ ተገዷል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን በተካሄደው ህዝባዊ ግምገማ ህዝቡ “ኢህአዴግ የ ችግርና መከራ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ለአገሪቱ ያመጣም ምንም ነገር የለም” በማለት በድፍረት መናገሩን ዘጋቢያችን ገልጧል።
በተለይ የደብረ ኤሊያስ አካባቢ የመኢአድ ደጋፊዎች “ተቃውሞዓችን በሙስና ከተዘፈቀ ስርአት ጋር ነው” የሚል መልክት ለህዝቡ ሲያስተላልፉ እንደነበር ተገልጧል።
የአካባቢው ህዝብም በኢህአዴግ ባለስልጣናት ላይ የስድብ ውርጅብኝና “እናንተ አትመሩንም ፣ በቃችሁ ውረዱ ” የሚል መልክት ሲያሰማ ነበር ።
በጎንቻና መርጦ ለማርያም እንዲሁ ተመሳሳይ መልክቶች በመሰማታቸው፣ የአካባቢው አመራሮች ተቃዋሚዎች ህዝቡን በማነሳሳት መድረኩን የቅስቀሳ አድርገውታል በሚል በዞኑ የሚካሄደው ግምገማ እንዲቋረጥ ተድርጓል።
በእያንዳንዱ የወረዳና ዞን አመራር ላይ ህዝቡ አስተያያት እንዲሰጥበት መደረጉን የገለጠው ዘጋቢያችን፣ “ህዝቡ አመራሩን ” አንፈልጋችሁም፣ ሙሰኞች ናችሁ” እንዳላቸውና አንዳንድ አመራሮችም መድረክ ላይ እርስ በርሳቸው ሲወቃቀሱ እና ሲካሰሱ እንደነበር ገልጧል።ግምገማው እንዲቆም የተደረገውም ከበላይ አካል በመጣ ትእዛዝ ነው።
የግምገማው አላማ ይፈነዳል ተብሎ የታሰበውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማብረድ ቢሆንም፣ ችግሩን ከማባባስ ውጭ የፈየደው ነገር አለመኖሩን ዘጋቢያችን ገልጧል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ብአዴን ስድስት ከፍተኛ አመራሮችን ማገዱም ተሰምቷል። አመራሮቹ የታገዱት በሙስና ሰበብ ይሁን እንጅ በፓርቲው ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠረ በመጣው የፖለቲካ ልዩነት መሆኑን ታማኝ ምንጮች ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምስራቅ ጎጃም ዞን የብአዴኑ ሊቀመንበር የአቶ ደመቀ መኮንንና የአቶ በረከት ስምኦን የቀኝ እጅ ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩት በምስራቅ ጎጃምና አዊ ዞን የጸረ ሙስና ሃላፊ በመሆን እና በተዘዋዋሪም የዞኑ አራጊ ፈጣሪ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ የሺጥላ እምሩ ከስራ መታገዳቸው ታውቋል። ግለሰቡ በምርቻ 97 ወቅት ኢህአዴግ በምስራቅ ጎጃም ዞን ባሉ ወረዳዎች መሸነፉን አንዳንድ የወረዳ ፍርድቤቶች ቢወስኑም ውሳኔው ተሽሮ ኢህአዴግ እንዳሸነፈ ተደረጎ እንዲቆጠር ያደረጉ ነበሩ።
ለግለሰቡ መታገድ ሰበቡ ሙስና ይሁን እንጅ የአካባቢው ህዝብ በግለሰቡ ላይ የሚያሰማው እሮሮ ብአዴንን ስላስደነገጠው የተወሰደ እርምጃ ነው ተብሎአል።
በደቡብ ወሎ ዞን ከግምገማ ጋር በተያያዘ በርካታ የብአዴን አባሎች መባረራቸውን እንዲሁም ሁለት የካቢኔ አባሎች እርስ በርስ በሽጉጥ መጋደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ ከ180 በላይ የብአዴን አባላት ድርጅቱን ለቀው ወጥተዋል። አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በብአዴን ውስጥ የሚታየው ትርምስ፣ የድርጅቱን ህልውና ወደ ፍጻሜ የሚያደርሰው ነው።