ጥቅምት ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ታሪካዊውን ምርጫ 97ትን ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት የሞቱ ሰማእታት 7ኛ አመት በተለያየ መንገድ እየታወሰ ነው።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ልዩ ግምት የሚሰጠው ምርጫ 97 የኢትዮጵያውያንን የዲሞክራሲ እና የነጻነት ህልም ያጨለመ እንደነበር በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች እና አለማቀፍ ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።
በምርጫው ማግስት በተፈጠረው ግጭት ከ200 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ1 ሺ ያላነሱት ደግሞ መቁሰላቸውን እንዲሁም ከ30 ሺ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።
በተለይ አጋዚ እየተባለ የሚጠራው ልዩ የመከላከያ ሀይል በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች ላይ በፈጸመው ጭፍጨፋ በርካቶች ፖለቲካን እርግፍ አድርገው እንዲተው አድርጓቸዋል። በጭፍጨፋው የተሳተፉ ባለስልጣናትም ሆኑ ወታደሮች እስከዛሬ ለፍርድ አልቀረቡም።
ኢሳት የዛሬውን ስርጭት ሰማእታቱን የተመለከቱ ዝግጅቶችን በማቅረብ እየዘከረ ነው።