(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 13/2010)የምህረት አዋጁ ጸደቀ።
የምህረት አዋጁ በተለያዩ ወንጀሎች የተከሰሱና የሚፈለጉ እንዲሁም የተፈረደባቸውን ሰዎች ጭምር ነጻ የሚያደርግ መሆኑም ታውቋል።
ፓርላማው በአስቸኳይ ስብሰባው ያጸደቀው የምህረት አዋጁ ከግንቦት 30/2010 በፊት በወንጀል የሚፈለጉና የተፈረደባቸው እንዲሁም የተከሰሱ ሰዎችን ሙሉ በሙሉ ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
የምህረት አዋጁ የኮበለሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትንም ነጻ የሚያደርግ ይሆናል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ የጸደቀው ይህ የምህረት አዋጅ፣የንብረት መወረስን የማይጨምር መሆኑም ተመልክቷል።
የምህረት አዋጁ ከግንቦት 30/2010 ወዲህ የተፈጸሙ ድርጊቶችን ግን አይመለከትም ተብሏል።
በፖለቲካ ተሳትፏቸው ሳቢያ የተሰደዱና ሌሎችንም ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ያበረታታል የተባለው ይህ የምህረት አዋጅ የተከሰሱና የተፈረደባቸውን ብቻ ሳይሆን ጉዳያቸው በምርመራ ላይ ያሉ ግለሰቦችን ጭምር ከተጠያቂነት ሙሉ በሙሉ ነጻ እንደሚያደርግም ይፋ ሆኗል።
በመደበኛ ፍርድ ቤትም ይሁን በወታደራዊ ፍርድቤት ጉዳያቸው የሚታይና የታየ ግለሰቦችንም በነጻ የሚያሰናበተው የምህረት አዋጅ ሰራዊቱን ጥለው የኮበለሉ ወታደሮችንም ሆነ ሌሎች ባለማዕረጎችንም ከተጠያቂነት ነጻ ያደርጋል።
ይህ የምህረት አዋጅ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ ዛሬ መጽደቁ ተገልጿል።
በምህረቱ የማይካተቱ ወንጀሎችን በተመለከተ ግን የወጣ ዝርዝር ማብራሪያ የለም።