(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 18/2010) አዲስ የወጣው የምህረት አዋጅ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩና የተከሰሱ እንዲሁም የተፈረደባቸውን ሰዎች እንደማይጨምር ተገለጸ።
ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሙስና ማለትም በሌብነት ወንጀል የሚጠየቁና የተጠየቁ ግለሰቦች የምህረት አዋጁ አይመለከታቸውም።
ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ብርሃኑ ጸጋዬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እስከ ግንቦት 30/2010 ድረስ ያለውን ጊዜ ብቻ በሚሸፍነው የምሕረት አዋጅ ምህረቱ የሚመለከታቸው ሰዎች ተመዝግበው ሰርተፍኬት መያዝ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
በዚህ የምህረት አዋጅ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ሪፖርት ያላደረጉ ሰዎች የመብቱ ተጠቃሚ እንደማይሆኑም አመልክተዋል።
ሪፖርት ማድረጉ ያስፈለገው ለሰዎቹ ሰርተፍኬት ለመስጠትና በተለይ ከውጭ ሲመጡ መጉላላት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል ነው ብለዋል።
ሆኖም ይህ የምህረት አዋጅ በሌብነት ማለትም በሙስና በሚፈለጉ፣የታሰሩና የተፈረደባቸውን ሰዎች እንደማይጨምርም ግልጽ አድርገዋል።